ባህር ዳር ዩንቨርስቲ የክልሉ ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ መደበኛ ተማሪዎችን አስገብቶ ለማስተማር አያስችልም አለ።

አሸናፊ አሰበ

16/04/2016

በአማራ ክልል የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለነባር እንዲሁም አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎቻቸው ጥሪ ሳያደርጉ አራት ወራት ተቆጥረዋል።

ተማሪዎችም ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመድባቸውና ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጉትጎታ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ግን በአማራ ክልል የሚገኙ አስሩም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ጠርተው ትምህርት እንዲያስቀጥሉ እንደተነገራቸው እና ተቋማቱም በቅርቡ ጥሪ ለማድረግ መስማማታቸውን ይናገራል።

ይህንንም ተከትሎ አዲስ ጊዜ ትምህርት መቼ ለመጀመር እንዳቀዱ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ግርማው አሸብርን ጠይቃለች።

አንደ አቶ ግርማ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በማንኛውም ሰዓት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑንና በአሁኑ ሰዓትም በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የድሕረ ምረቃ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸው ነገር ግን አሁንም መደበኛ ተማሪዎችን ጠርቶ ትምህርት ለማስቀጠል ክልሉ ያለበት ሁኔታ አያስችልም ብለዋል።

የክልሉ ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ተማሪዎችን ጠርቶ ለማስገባት አንዳንድ መንገዶች ክፍት አለመሆናቸውን ገልጸው ተማሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቢገቡ እንኳን የተማሪዎችን ምግብ ለማስገባት ሁኔታዎች አስቸጋሪ መሆናቸውን አክለዋል።

ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ሁኔታዎችም ተረጋግተው መንግስት ሰላሙ አስተማማኝ ነው ካለ እና የተማሪዎች ህይወት አደጋ ላይ የማይጥል ሁኔታ ከተፈጠረ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ጫና እና ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንደሚኖሩበት እንረዳለን ያሉት አቶ ግርማው ነገር ግን አማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቋርጧል የክልሉ ሰላምም በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ ትምህርት ለማስቀጠል አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስቀጠል አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ፤ ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ መንግሥት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ክልሉ እና በክልሉ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት በጋራ ይሠራሉ ሲል አስታውቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ ምን ምን እገዛዎችን እንደሚያደርግ በዝርዝር አልገለፀም።ይህንን ለማካተት የትምህርት ሚኒስቴር አካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኤባ ሚጀና ጋር ደጋግመን ብንደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት ሳንችል ቀርተናል።