ገና-ተዋህዶ ኤክስፖ ያጋጠመው ምንድነው?

አሸናፊ አሰበ

16/04/0216

ማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው እና ከታህሳስ 11-27/2016 ዓ.ም በጃንሜዳ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ገና ተዋህዶ ኤክስፖ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ቢሮ ፍቃድ ባለመስጠቱ ምክንያት መካሄድ እንዳልቻለ የማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ባለቤት ኤፍሬም አደፍርስ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።

ይጀምራል ተብሎ ማስታወቂያ ከተነገረበት ቀን በ አምስት ቀናት የዘገየው ኤክስፖው እስካሁን ፍቃድ የሚሰጠው አካል ባለማግኘቱ የሚካሄድበት ቀን አልታወቀም።

የሚካሄድበት ቀን ከመድረሱ ቀደም ብሎ ወደ ጽ/ቤቱ ፍቃድ ለማግኘት ብዙ ተመላልሰናል ያሉት አዘጋጆቹ ዛሬ ነገ ስንባል ቀኑ በመድረሱ ምክንያት ነጋዴዎች ወደ ጃንሜዳ እንዲገቡ ፈቅደን ነበር ያሉ ሲሆን ነጋዴዎች መግባት ከጀመሩ በኋላ በፖሊስ እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የሰላም እና ጸጥታ ጽ/ቤቱ ፍቃድ ለመስጠት ቀጠሮ እንዳበዛባቸው የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ፕሮግራሙ መካሄድ ካለበት ቀን እየገፋ ነው ያሉ ሲሆን ጽ/ቤቱም ፍቃድ ለመስጠት ለምን ዳተኛ እንደሆነ ጥያቄ ፈጥሮብናል ብለዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ቢሮው ብንመላለስም ፍቃድ የሚሰጠን አካል አጥተናል ያሉት አቶ ኤፍሬም ማስታወቂያ የሰሙ ሸማቾችም ጃንሜዳ እየደረሱ እየተመለሱ ነው ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ቢሮ ምላሽ እንዳገኘን የምናካትት ይሆናል።