በኦሞ ወንዝ መሙላት ምክንያት የተፈጠረው ጎርፍ 123ሺ ሄክታር የግጦሽ መሬት ሸፍኗል ።

አሸናፊ አሰበ

16/04/2016

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ከሚገባው በላይ በመሙላቱ ምክንያት በተፈጠረው ጎርፍ 79,828 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በ 12 መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ እና ጎርፋም  123ሺ ሄክታር የግጦሽ መሬት ላይ ተኝቶ እንዳለ የወረዳው የአደጋ ስጋት ቅነሳ እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሰኢድ ለአዲስ ጊዜ ገለጹ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ 6 አርብቶ አደር ወረዳ እና አንድ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሲሆን 16ሺ እማውራ እና አባውራ(ቤተሰቦች) በጎርፉ ምክንያት መፈናቀላቸው ተሰምቷል ።

ከ 2012 ዓ.ም አንስቶ በተደጋጋሚ በወረዳው እየተከሰተ ያለው ጎርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ነዋሪዎችን ይማረረ ሲሆን ተፈናቃዮች በአሁኑ ሰዓት ተጠልለው በሚገኙበት መጠለያ ጣብያ ቋሚ ኑሮ ለመመስረት መንግስት ጠይቀዋል ተብሏል።

በማእከላዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚዘንበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የኦሞ ወንዝ ከሚገባው በላይ በመሙላቱ ምክንያት በወረዳው ከሚገኙ 40 አጠቃላይ ቀበሌዎች ውስጥ 34ቱን እንዳፈናቀለ ሃላፊው ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ ለተጨማሪ ጉዳት በማይዳረጉበት ሁኔታ ከ ወንዙ ከ 11-12 ኪሜ ርቀት ላይ መስፈራቸው ተገልጿል።

የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ከወጣበት እና ጉዳት ካደረሰበት ጥቅምት 16/2016 ዓም አንስቶ በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት በ 34 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ የግብርና ጣቢያዎች ፣የእንስሳት ህክምና ተቋማት፣ የእንስሳት መኖ፣ ግምጃ ቤቶች እና የህክምና ተቋማት ከነ ሙሉ ቁሳቁሳቸው መውደሙን ሃላፊው አክለዋል።

እስከ ጥር ድረስ ዝናቡ ይቀጥላል የሚል ትንበያ በሜትርሎጂ ኤጀንሲ በመኖሩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረጉ እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው ተፈናቃዮች አሁን በሚገኙበት ቦታ በቋሚነት እንዲኖሩ እየሰሩ መሆኑን አክለዋል።

ከወረዳው ማዕከል እስከ መጠለያ ጣቢያዎች ከ 7-64 ኪሜ ርቀት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ኡስማን መንገዶች አሸዋማ በመሆናቸው እና ለመኪና መንገድ ምቹ ባለመሆናቸው በተለይም ንጹህ ውሃ የማድረስ ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል።
Website |Youtube|Telegram|Facebook|Tiktok|Twitter /x/

Addis Gize -አዲስ ጊዜ, [26/12/2023 16:42]
ገና-ተዋህዶ ኤክስፖ ያጋጠመው ምንድነው?

አሸናፊ አሰበ

ማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው እና ከታህሳስ 11-27/2016 ዓ.ም በጃንሜዳ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ገና ተዋህዶ ኤክስፖ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ቢሮ ፍቃድ ባለመስጠቱ ምክንያት መካሄድ እንዳልቻለ የማርኮናል ኤቨንት ኦርጋናይዘር ባለቤት ኤፍሬም አደፍርስ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።

ይጀምራል ተብሎ ማስታወቂያ ከተነገረበት ቀን በ አምስት ቀናት የዘገየው ኤክስፖው እስካሁን ፍቃድ የሚሰጠው አካል ባለማግኘቱ የሚካሄድበት ቀን አልታወቀም።

የሚካሄድበት ቀን ከመድረሱ ቀደም ብሎ ወደ ጽ/ቤቱ ፍቃድ ለማግኘት ብዙ ተመላልሰናል ያሉት አዘጋጆቹ ዛሬ ነገ ስንባል ቀኑ በመድረሱ ምክንያት ነጋዴዎች ወደ ጃንሜዳ እንዲገቡ ፈቅደን ነበር ያሉ ሲሆን ነጋዴዎች መግባት ከጀመሩ በኋላ በፖሊስ እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የሰላም እና ጸጥታ ጽ/ቤቱ ፍቃድ ለመስጠት ቀጠሮ እንዳበዛባቸው የተናገሩት አቶ ኤፍሬም ፕሮግራሙ መካሄድ ካለበት ቀን እየገፋ ነው ያሉ ሲሆን ጽ/ቤቱም ፍቃድ ለመስጠት ለምን ዳተኛ እንደሆነ ጥያቄ ፈጥሮብናል ብለዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ቢሮው ብንመላለስም ፍቃድ የሚሰጠን አካል አጥተናል ያሉት አቶ ኤፍሬም ማስታወቂያ የሰሙ ሸማቾችም ጃንሜዳ እየደረሱ እየተመለሱ ነው ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት የሰላም እና ጸጥታ ማስከበር ቢሮ ምላሽ እንዳገኘን የምናካትት ይሆናል።

Website |Youtube|Telegram|Facebook|Tiktok|Twitter /x/