4ኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሸ ድርድር ያለውጤት ተጠናቀቀ

10/04/16

አሸናፊ አሰበ

ኢትዮጵያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያለውን ልዩነት በመፍታት ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ ስምምነት ለመድረስ ፍላጎት ብታሳይም ግብጽ በግድቡ ላይ እስካኹን በተደረጉት ድርድሮች ባራመደችው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ከስምምነት ላይ ሳይደረስ ቀርቷል ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ገለጸ።

በግድቡ የውሃ አሞላል ላይ እና በግድቡ አስተዳደር ላይ ኢትዮጵያ ለድርድር የተቀመጠችው ከሀገራቱ ጋር መተማመን ማስፈን እንጂ የሀገሪቱን በአባይ ውሃ ላይ የመጠቀም እና የመልማት መብት ለመገደብ አይደለም ሲል አቋሙን ያንጸባረቀው መግለጫው ኢትዮጵያ አሁንም በግልጽ ማስቀመጥ የምትፈልገው ዋነኛ ጉዳይ የአሁኑን እና የቀጣዩን የሀገሪቱን ትውልድ ተጠቃሚ በሚያደርግ እና የእኩልነትና ምክንያታዊነት መርሆችን ባከበረ አኳኋን የወንዙን ውሃ መጠቀሟን ትቀጥላለች ብሏል።

አራተኛው የሶስትዮሽ ድርድር መጠናቀቁን ተከትሎ የግብጽ መንግስት ያወጣውን መግለጫ የተቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመንግስታቱ ድርጅትን እና የአፍሪካ ህብረት ቻርተሮችን የጣሰ እንዲሁም የኢትዮጵያን አቋም አዛብቶ ያቀረበ ነው ሲል ኮንኗል።