10/04/2016
ለዓለም አሰፋ
መንግስት ከፋኖ መሪዎች ጋር ይነጋገር ሲል ክራይሲስ ግሩፕ ጥሪ አቀረበ።
በምዕራብ ሀገራት ባሉ ፖሊሲ አውጭዎች ተደማጭነት ያለው የሀሳብ አመንጭ ተቋም ክራይሲስ ግሩፕ የአማራ ክልል ግጭት በአፋጣኝ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ ለሀገሪቷ አደገኛ ይሆናል ብሏል።
ተቋሙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ነፍጥ ካነገቡ የክልሉ ታጣቂዎች ጋር እንዲደራደሩ ምክር ለግሷል። መቀመጫውን በቤልጂየሟ መዲና ብራስልስ ያደረገዉ መንግስታዊ ያልሆነዉ ይህ ተቋም በዓለም ዙርያ ያሉ ቀውሶችን በመመርመር ትንታኔዎችን ያቀርባል፤ በመንግስታት ፖሊሲ አርቃቂዎች፥ በምሁራን እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ትንታኔዎቹ ተደማጭነት አላቸው።
ድርጅቱ የአማራ ክልል ግጭትን አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሦስቱ ክልሎች በኦሮሚያ፥ በትግራይ እና አሁን ደግሞ በአማራ መንግስትን የሚቃወሙ የትጥቅ እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውን ጠቅሶ፥ ግጭቶቹ በብሔሮች መካከል ያሉ የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን አሻክረዋል ብሏል። ይህም አገሪቷን መረጋጋት እንዲርቃት የሚያደርግ ነው ሲል አክሏል።
መንግስት በተለያዩ ክልሎች የሚነሱ እና እርስ በእርስ የተቆላለፉ ግጭቶችን ለመፍታት ውይይትን ሊያስቀድም ይገባል ሲል ምክረ ኃሳብ አቅርቧል። መንግስት ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ውይይቶችን እንዲያደርግ ጫና ሊያደርጉበት ይገባል ሲልም ለአፍሪካ መሪዎች፥ ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ኅብረት ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ክልል ያለው ያለመረጋጋት በአገሪቷ ተስፋፍቶ ያለውን ነውጥ ማስቆም ችግር ለሆነባቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ ሌላ የራስ ምታት መሆኑን ገልፆ በተለይም ደግሞ ግጭቶቹ እያሽመደመዱት ያለው የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት በቶሎ እንዳያገግም ደንቃራ ይሆናልም ብሏል። ክራይሲስ ግሩፕ እንደሚለው ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ዋልታ የነበረችው ኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብቷ የሞት አፈፋ ላይ ደርሶ በጊዜያዊ ማስተፈንሻ ብቻ እያጣጣረች መሆኑን ገልጿል።
ምንም እንኳ በአማራ ክልል ለተነሱበት የፋኖ ሀይሎች መንግስት ወታደራዊ ዘመቻን እንደመፍትሔ እየወሰደው ያለ ቢመስልም፥ ዘመቻውም ብቻውን የሚፈለግለትን ውጤት ያስገኛል ብሎ እንደማያምን ተቋሙ ጨምሮ ተናግሯል። ከዚያ ይልቅ ዋና ዋና ከሚባሉ የታጣቂ መሪዎች ጋር ውይይት እንዲያደርግ መክሯል። በተራዛሚ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ አገር አቀፍ የእርቀ ሰላም ዕቅድ ቢነደፍ ይበጃልም ብሏል።
የፋኖ ሀይሎች የደፈጣ ጥቃትን እንደውጊያ ስልት መከተል በመያዛቸው እና የህዝብ ድጋፍ ያላቸዉ በመሆኑ የመንግስት ወታደራዊ ዘመቻዎች ስኬታማነትን ጥያቄ ውስጥ የገባ ነዉ ያለዉ ተቋሙ እነዚህ የውጊያ ስልቶችም ወደለየለት የፊት ለፊት ጦርነት ይቀየራሉ ለሚለዉ ጊዜ ምላሽ ይኖረዋል ሲል አስታዉቋል።
ይሁንና የተራዘመ ግጭት ሊኖር እንደሚችልና ይህም ለሀገሪቷ አስጊ እንደሆነ ገልጿል።
