በትላንትናው ዕለት ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትስር ዴኤታነታቸው የተነሱትአቶታዬደንደአ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጸጥታናደህንነት የጋራ ግብረኃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ታህሳስ02/2016

ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲሰሩ የቆዩት አቶ ታዬ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጻፈ ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ትላንት ሰኞ ታህሳስ 1፤ 2016 ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ሚኒስትር ዴኤታው ከስልጣናቸው የተነሱበትን ምክንያት ባይጠቅስም፤ ይህንኑ ተከትሎ አቶ ታዬ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት ጹሁፍ ግን ከስልጣናቸውን የተነሱት “የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገናቸው” መሆኑን አስፍረው ነበር። 

የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ በዛሬው መግለጫው፤ አቶ ታዬ በተመደቡበት ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ሆነው መንግስትን “ገዳይ እና ጨፍጫፊ” እያሉ “በተደጋጋሚ ሲወቅሱ” መደመጣቸውን ጠቅሷል። ሆኖም በተግባር “ከሽብርተኞች፣ ጽንፈኞች እና ነፍሰ ገዳዮች ጋር” በተግባር “የጥፋት ትስስር የነበራቸው” ራሳቸው አቶ ታዬ መሆናቸውን “በተደረገ ክትትል መረጋገጡን” የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አስታውቋል። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ተቀብለው እየሰሩ ባሉበት ወቅት “መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡዕ  እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል” ሲል የሚከስሰው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ ይህንኑ በመረዳትም በአቶ ታዬ ላይ “ያላሰለሰ ጥናት እና ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር” አትቷል።

በተደረገው ክትትልም አቶ ታዬ “ከኦነግ ሸኔ አመራሮች እና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር” መንግስትን “በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል” ሲል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው ወንጅሏል። አቶ ታዬ በህግ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት “በህቡዕ ለሚያደርጉት ጸረ-ሰላም እንቅስቃሴ ሲገለገሉባቸው ነበር” የተባሉ “ሞባይሎች፣ ላፕቶፖች፣ አይፖዶች፣ ፍላሾች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪ ሰሌዳዎች” በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ “ፍተሻ” መገኘታቸውን መግለጫው አመልክቷል። 

በዚሁ ፍተሻ “ክላሽንኮቭ ጠመንጃ እና ሽጉጦች” “ከመሰል ጥይቶች ጋር” መገኘታቸውን ያስታወቀው የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ “የኦነግ ሸኔ አርማዎች” እና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ “የኦነግ ሸኔ መታወቂያዎች፣ ሰነዶች እና ማስታወሻዎች” መያዛቸውንም ገልጿል። በአቶ ታዬ መኖሪያ ቤት በተደረገው ፍተሻ ወቅት፤ “የኦነግ ሸኔ አባል ነው” የተባለ ግለሰብ “ተደብቆ መገኘቱን” በቁጥጥር ስር መዋሉን የጋራ ግብረ ኃይሉ አክሏል።

የእርሳቸው አይነት አቋም በሌሎች ሚኒስትሮች እና ባለስልጣናትም ዘንድ ያስተውሉ እንደሆነ በ“ኢትዮ ፎረም” የተጠየቁት አቶ ታዬ፤ “በጣም ብዙ ሰው ብዙ ነገር መበላሸቱን እያየ ለመወሰን የተቸገረ እንዳለ አውቃለሁ። ግን ጉዳዩ ውሎ አድሮ የሚታይ ነው የሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተው ነበር። የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዛሬው መግለጫው ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።