03/2016

በተለይ ባለፉት አራት አመታት በቀጠናው ክፉኛ የአንበጣ መንጋ ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የማዕከሉ ሪፓርት አመላክቷል። በጎረቤት ኬንያ ምዕራባዊ ክፍል በተገባደደው የፈረንጆቹ 2023 ብቻ 5.5 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት እህል በወፎች ወድሟል። ይህም በቶን ሲሰላ 60ቶን ገደማ ነው ተብሏል።
ይህ ይፋ የተደረገው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል ICPAC ከኢጋድ አባለ ሀገራት ለተወጣጡ ጋዜጠኞች በሰጠው ስልጠና ላይ ነው። ስልጠናው በዋናነት የበረሃ አንበጣና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ፀረ ሰብል ተባዮች ላይ ያተኮረ ነው።
በወፎች ከሚጠቁ የሰብል አይነቶች ውስጥ ማሽላ፣ስንዴ፣ሩዝ ጤፍ እና ገብስ በግባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።የሙቀት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ለተባዮች መፈልፈል እና መራባት አስተዋፅዎ የሚያደርግ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ለዚህ ችግር ግዙፉን ድርሻ ይይዛል ሲሉ የICPAC-IGAD የምድር ምልከታ እና የጂኦ መረጃ ባለሞያ የሆኑት ኬኔት መዋንጊ ለአዲስ ጊዜ ገልፀዋል። እንደ ባለሞያው ገለፃ “በአረንጓዴ ተክል መሸፈኑ አከባቢዎች ለአንበጣ መስፋፋት አመቺ ናቸው ይሄም የአንበጣ መንጋ እና ፀረ ሰብል ተባዮች ስጋት ላለባቸው የቀጠናው ሃገራት ስጋት ነው” ብለዋል::

እንደ ኢጋድ የአየር ትንበያና ትግበራ ማዕከል መረጃ ከሆነ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2019 እስከ 2021 የበረሃ አንበጣን ለመከላከል 85ዐ ሚሊየን ዶላር ወጪ ተደርጓል። ይህም ገበሬው አምርቶ እንዳይሰበስብ ፈተና እንደሆነበት ነው የተነገረው። ኢጋድም በቀጣናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረበት ይፋ አድርጓል።
የኢጋድ አባል አገራት ቀጣናውን ማዕከል ያደረገ የመከላከል ሥራ ሊያከናውኑ ይገባል ተብሏል በዚህ ረገድ የሚዲያ ባለሞያዎች የችግሩን ስፋት በመረዳት ለማህበረሰቡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው የ ICPAC-IGAD የኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር የሆኑት ወይዘሮ እመቤት ጂግሳ ገልፀዋል።

