“ያደጉት ሃገራት የገቡትን ቃል እንደሚከውኑት ከአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው ይጠበቃል” አቶ ነመራ ገበየሁ

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ130 በላይ ሀገራት የሚሳተፉበት 28ተኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከህዳር 20 – ታህሳስ 2 በዱባይ እንደሚካሄድ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ነመራ ገበየሁ ገለጹ።

ጉባኤው በዓመት አንድ ጊዜ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተባባሪነት የሚዘጋጅ ሲሆን ኢትዮጵያን በሚወክለው ልኡክም ዝግጅት እንደተደረገ ተነግሯል።

በአጠቃላይ ለ12 ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ከህዳር 20 – 21 የሃገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ሲሆን መሪዎችም የሀገራቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎችን እንደሚያስተዋውቁ እና በመሪ ደረጃ ሊነሱ የሚገቡ የአየር ንብረት ለውጥ ፓሊሲዎችን እንደሚያስተዋውቁ ይጠበቃል። በቀሪው የጉባኤው ወቅትም መሪዎች በሚያስቀምጡት መመሪያ መሰረት ውይይቶች እንደሚቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

በጉባኤው እ.አ.አ በ2015 ተደርጎ በነበረው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የፓሪስ ስምምነት ግምገማ እንደሚካሄድ እና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድ (Adaptation plan) ላይ ግልጽ የሆነ አሰራር እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል።

ያደጉት ሀገራት እ.አ.አ እስከ 2020 ድረስ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በዓመት 100 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም እስካሁን እንዳልተፈጸመ ነገር ግን በርከት ያሉ ሃገራት በአየር ንብረት ለውጥ እየተጎዱ በመሆኑ ቃል አክብረው ልገሳውን ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በተጨማሪም፣ በጉባኤው ከተለያዩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ እና ኢትዮጵያም የታዳጊ ሀገራት ወይም በትንሹ የበለጸጉ ሀገራት (Least Developed countries) አካል እንደመሆኗ በዚሁ አደረጃጀት አየርን ንብረትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በጉባኤው እንደምታቀርብ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።