አንቶኒ ብሊንከን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ተወያዩ 

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል። በውይይታቸው ላይ በቀጣይ ወር በኢትዮጵያ ተቋርጦ ስለነበረው እና ዳግም ሊጀመር ስለታሰበው የምግብ እርዳታ አቅርቦት መምከራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ቢሮ ገልጿል።

ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግስት እና የሰብአዊ ዕርዳታ አጋሮች ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ለተጋለጡ ወገኖች የምግብ እርዳታ መድረሱን ለማረጋገጥ ያደረጉትን ማሻሻያ አድንቀዋል ተብሏል።

አንቶኒ ብሊንከን እና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላምን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት እና የቀጠናዊ ትብብር አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዋል ሲልም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ጨምሮ አስታውቋል።

በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንዳሳሰባቸው የገለጹት ሃላፊው ግጭቶችን ለመፍታት ውይይት እና ድርድር አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል በማለት ቢሮው አስታውቋል።