ዳዊት ታደሰ
የኢትዮጵያ ሰበአዊ መብቶች ኮሚሽን ህዳር 07 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ መንግስት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጠውት የነበረውን የምግብ እርዳታ መልሰው ለመጀመር መወሰናቸው የሚወደስ ነው ብሏል፡፡
ኢሰመኮ በመግለጫው፣ በትግራይ ክልል ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ከሰኔ ወር ጀምሮ የተቋረጠውን የምግብ እህል እርዳታ ተከትሎ ስለተፈጠረው ሁኔታ ክትትል ሲያደርግ እንደነበር ዘርዝሯል፡፡
ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ፍልሰተኞች በተለይ ደግሞ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ጋር ለመድረስ እንዲቻል አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ጨምሮ ሌሎች የማስተባበር ስራዎች በፍጥነት እንዲከወኑ ሲወተውት መቆየቱን ያስታወሰው ኮሚሽኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምገባው እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንዲወጡ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን ጠቅሷል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር የሆኑት ራኬብ መሰለ {በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ እርዳታ ለአንድ ዓመት ያክል እንዲቀጥል መወሰኑ በስፋት እጥረት የሚታይበትን ሰበአዊ ፍላጎት ለማርካት በጉልህ ይጠቅማል} ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የተጀመረው እርዳታ በአስፈላጊው ጊዜ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ቀሪ እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወሰዱም ጨምረው አሳስበዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የአሜሪካ መንግስት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤድ) በኢትዮጵያ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ለተረጂዎች ሳይደርስ ለሌላ ዓላማ ውሏል በማለት ማቋረጡን ተናግሮ ነበር፡፡ በወቅቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የእርዳታው ላልተገባ ጥቅም መዋልን አመላክቶ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱን አስምሮበታል፡፡
