ዩ.ኤስ.ኤድ ያቋረጠውን ርዳታ ሊጀምር ነው

ዩኤስኤድ ከወራት በፊት አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከቀጣይ ወር ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ እንደሚጀምር ማስታወቁ ተዘግቧል።በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጎጂዎች ተብሎ የሚቀርብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑ በመረጋገጡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡ ይታወሳል።

ዩ.ኤስ.ኤድ በመላ ሀገሪቱ ለአንድ አመት ያክል የእርዳታ ስርጭቱን በማካሄድ ለመሞከር ማቀዱን አስታውቋል ያለው የሮይተርስ ዘገባ በዚህ የሙከራ ጊዜ የምግብ እርዳታውን አቅርቦት ለሚገባቸው ተረጂዎች መዳረሱን ክትትል እንደሚያደርግ እና ምርምራ እንደሚያከናውን መግለጹን አመላክቷል። የረድኤት ድርጅቱ የምግብ አቅርቦቱን የሚጀምረው ለበርካታ ወራት ከመንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች ከተከናወኑ በኋላ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው የኢትዮጵያ መንግስት እና አጋር አካላት ከእርዳታ እደላ ጋር በተያያዘ እጅግ አስፈላጊ ማሻሻያዎች በማከናወናቸው መሆኑን አስታውቋል።

የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎችን በመለየቱ ረገድ የረድኤት ድርጅቶች ሀላፊነቱን ወስደው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ መንግስት መስማማቱን የጠቆመው ዘገባው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ እርዳታ የሚከፋፈልባቸውን ቦታዎች ያለምንም ገደብ ዩኤስኤድ እና የረድኤት ድርጅቶቹ እንዲጎበኙ እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ መፍቀዱን አስታውቋል።ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ሀገሪቱ በትግራይ ተካሂዶ በነበረው ጦርነት እና ከበርካታ አመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተከሰተው ድርቅ ኢትዮጵያ የምግብ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን ዘገባው አትቷል።

የረድኤት ተቋሙ የእርዳታ አቅርቦቱን ለማስጀመር ውሳኔ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ላይ ለሚካሄደው የእርዳታ ማጓጓዝ፣ ማከማቸት እና ማከፋፈል ዙሪያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይኖረው ስምምነት ላዮ በመደረሱ መሆኑን የዩኤስኤድ ቃል አቀባይ እንደገለጹለት የዜና አውታሩ በዘገባው ማስታወቁም ተካቷል።