የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፓርላማ ውሎ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን ህዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዶ ነበር።

የምክር ቤት አባላትም ማብራሪያ ቢሰጥባቸው ያሏቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይም ምላሽ ያሉትን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በብዙዎች ዘንድ አወዛጋቢ በተባለ በዚህ ገለፃቸው ላይ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን አዲስ ጊዜ ሚዲያም አንኳር ነጥቦቹን እንዲህ አሰናድታዋለች፡፡

መንግሥትን በኃይል ስለመገዳደር

ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ትጥቅን የቀላቀሉ ትግሎችን የሚመለከተው አንደኛው ሲሆን በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ወደሰላም ለማምጣት ምን እየተደረገ እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠ/ሚንስትሩ ምላሻቸውን ሲጀምሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መንግሥትን በክላሽ ፈፅሞ መጣል አይቻልም” በማለት ነበር፡፡

“ከክላሽ ይልቅ ብእርና ሃሳብ ይዘን ለመወያየት ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡ በመገዳደል ልናሳካው የምንችለው ዓላማም ሆነ የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጀው በውይይት የበለጸገች አገር መገንባት ነው” ሲሉም አክለዋል። ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ ታጥቀው፣ ተዋግተው መንግስትን ያሸነፉ ሐይሎች የሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታገሉ አካላት ይህን ታሪክ በደንብ የሚያውቁ አይመስለኝም ብለዋል፡፡

 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የምክር ቤት ማብራሪያቸው ‹‹በእኛ ዕቅድ፣ ፍላጎት አንድም ጦርነት አልተካሄደም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹አንድም ግጭት እኛ አስበን፣ ጀምረን አናውቅም›› ያሉት ዐቢይ ‹‹ያም ይነሳል በሦስት ወር እንገለብጣችኋለን ይላል፤ ያም ይነሳል ሁለት ወር ይበቃኛል ይላል፤ ያም ይነሳል ይሄን መንግስት በቀላሉ በሀይል ልገለብጠው እችላለሁ ይላል›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ንግግራቸውን በመቀጠልም ‹‹መቼም አልሞት ባይ ተገዳይ ሆነን እንከላከላለን እንጂ እስካሁን ኢኒሼቲቭ ወስደን በራሳችን ተነሳሽነት ለማጥቃት ሙከራ አድርገን አናውቅም›› ሲሉ መንግስታቸውን ተከላክለዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ከዚህ ይልቅ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይዞት የመጣውን ዕድል እንዳያመልጠን እለምናለሁ እመክራለሁም” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ይሄ የብሔራዊ ምክክር እድል ለኢትዮጵያ መባከን የሌለበት፤ ካባከነው ሌላ ረጅም ጊዜ የሚጠይቀን ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ የምንቃወምም፣ የምንቃረንም፣ የምንፎካከርም፣ የምንታገልም ሁላችንም በሰከነ አእምሮ ይሄንን እድል ለመጠቀም መሞከር ይኖርብናል” ሲሉም ከምክር ቤት አባሉ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በሚመለከት

ዛሬ ሕዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት የተነሳው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ በአማራ ክልል ስለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱ በወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን መንግስት ከመፍረስ መታደግ ተችሏል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህም በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መጥቷል ሲሉም አክለዋል።

“በጉልበት የክልሉን መንግስት እናፈርሳለን ብለው የተነሱ ሃይሎች ነበሩ፡፡ የክልሉ መንግስትም የራሱን ሙከራ አድርጓል፡፡ ሳይሳካለት በመቅረቱ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ገብቶ አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ አድርጓል” በማለት የገለፁት ጠ/ሚንስትሩ የተሟላ ሰላም ባለመምጣቱ ግን ተጨማሪ ስራ እና ውይይት ይጠይቃል ብለዋል።

ይህንን ጥያቄ በመለሱበት ወቅት እግረ መንገዳቸውን መንግስታቸው በሕዝበ ውሳኔ ለመፍታት ስላሰበው የሰሜን ኢትዮጵያ አወዛጋቢ ቦታዎች አንስተዋል፡፡ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ያሉ አካባቢዎች የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ መንግስት እየሰራ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ነገር ግን የተሻለ መፍትሔ አለን ብሎ የሚመጣን አካል መንግስታቸው ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አክለዋል። “የአማራ እና ትግራይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተወያይተው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መፍትሔ አለን ካሉ በደስታ እንቀበላለን” በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡


ጠ/ሚኒስትሩ ስለፕሪቶሪያው ስምምነት

በፌዴራል መንግስቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ዘግናኝ ጦርነት የቋጨው የሰላም ስምምነት የፓርላማው ውሎ አንድ ገፅ ነበር። ስምምነቱ ስላለበት ደረጃ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከአንድ የምክር ቤቱ አባል የተጠየቁት ጠ/ሚንስትር ዐቢይ “የፕሪቶሪያው ስምምነት ቢያንስ ቢያንስ ለትግራይ እናቶች፣ ለኢትዮጵያ እናቶች እፎይታ ሰጥቷል፣ ቢያንስ ተጨማሪ ሰዎች እንዳይሞቱ አድርጓል” በማለት ስለጉዳዩ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።

ጨምረውም፣ “ከዚህ በተጨማሪ በገባነው ስምምነት መሰረት የኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት በስፋት እንዲጀመር አድርገናል፣ የክልሉ መንግስት ተቋቁሟል፣ በጀት ተፈቅዷል፤ ነገር ግን የቀሩ ስራዎች አሉ። የቀሩ ስራዎችን በትግራይ፣ በአማራ፣ በፌዴራል መንግስት በኩል በትብብርና ሰላምን በማስቀደም በውይይት እየተፈቱ ይሄዳሉ ብዬ አስባለው” ብለዋል።

“ቀሪ ስራ ስላለ ካልተዋጋን፣ ወደነበረው ካልተመለስን ካልን ግን ጥፋት ነው። የነበርንበት ከሁሉ የከፋ ነው፣ የቀረ ካለ ደግሞ በውይይት፣ በምክክር እየፈታን መሄድ ያስፈልጋል” ሲሉ ከፊል ማሳሰቢያ የተቀላቀለበት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የትምህርት ስርዓቱ ጉዳይ

ከፈተና ውጤት ጋር ተያይዞ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ የነበረው የትምሕርት ስርዓቱ ጉዳይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነሳ ሌላው አጀንዳ ነበር፡፡

“የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ ዘርፈ ብዙ ስብራቶች አሉበት፡፡ ስብራቶቹም በብዙ መንገድ ተንፀባርቋል፡፡ ይህን ለማቃናት ግን ብዙ ድካም ይፈልጋል፡፡” በማለት ምላሻቸውን የጀመሩት ጠ/ሚንስትር ዐቢይ “ዘርፈ ዘርፈ ብዙ ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡ ይህንን ለማሻሻል በለውጡ ማግስት የቀረፅነው የትምህርት ስርዓት ፍኖተ ካርታ ከሚያካትታቸው ነገሮች ውስጥ ካሪኩለም (ስርዓተ ትምህርት) መቀየር፣ የመምህራን አቅም መገንባት፣ ማሰልጠን እና ማሻሻል፣ የትምህርት አስተዳደር ስርአት መቀየር እና ማስፋፋት፣ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የፈተና ስርአቱን ማሻሻል፣ የተማሪዎች ምገባ መጀመር፣ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ መስራት ይገኙበታል” ብለዋል። “ነገር ግን ፈተናው ላይ ያለው ውጤት የሚጠበቅ ነው፡፡ ፈተናው ላይ ቁጥጥሩ ጨመረ እንጂ የትምህርት ስርዓቱ አልተቀየረም” ሲሉ አክለዋል።

 ውጤቱን በሚመለከት ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች በቀጣይ ዩኒቨርስቲ ገብተው ይማራሉ አልን እንጂ ከዚያ በታች ያመጡ ተማሪዎች ይቅሩ አልተባለም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ “አምናም ዘንድሮም የአቋም ማሻሻያ ወስደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አድርገናል ይደረጋልም፡፡ ምክንያቱም ውጤቱ የሚጠበቅ ስለነበር” ብለዋል።

D/r abiye ahmed
የወደብ እና የባሕር በር ጉዳይ

ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ እጅግ አነጋጋሪ የሆነው እና ምናልባት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ደም አፋሳሽ ወደሆነ ጦርነት እንዳያስገባን በሚል ሲያሰጋ የነበረው የባሕር በር ጉዳይ እንደተጠበቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጥያቄ መልክ ተነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ የቀጠናው ሀገራት በየተራ መግለጫ ያወጡበት ይህን አጀንዳ ጠ/ሚንስትሩ ሲያነሱ “የወደብ ጉዳይን አዲስ ጥያቄ አድርገው የሚያነሱት ቀደም ብለን የባሕር ሀይል መገንባታችንን የዘነጉ ናቸው” በማለት ነበር፡፡ ወደብን በሚመለከት ብዙ ትንተና እና ሴራዎች እየተሰሙ እንደሆነ የተናገሩት ጠ/ሚንስትር ዐቢይ ጎረቤት ሀገራት ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበትን ችግር በአንክሮ እንዲያጤኑ አሳስበዋል፡፡