የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለውን የምግብ ድጋፍ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት (USAID) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የምግብ ድጋፍ ለስደተኞች እንዲጀመር ማድረጋቸው በጎ እርምጃ ሆኖ፤ በአንጻሩ ለተፈናቃዮች እና ለሌሎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚሰጠው የምግብ ድጋፍ አቅርቦት እገዳ አለመነሳቱ በምግብ እጥረትና ሰብአዊ ቀውስ ላይ ያሳደረው ጫና እንደቀጠለ ነው ብሏል::
የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የተሟላ እና በቂ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ቢኖርም፣ ባለፉት ወራት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች ትኩረት በመስጠት በሁለት ዙር በአፋር ክልል 96%፣ በጋምቤላ 96%፣ በትግራይ 87%፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 73%፣ በሶማሊ 52%፣ በአማራ 43% የሰብአዊ ድጋፍ ማደረጉን አስታውቋል።
የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት በአፋር ክልል 290 ሺህ የሚሆኑ፣ በትግራይ ክልል 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ፣ በአማራ ክልል 1.9 ሚሊዮን እንዲሁም በኦሮሚያ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው ክልሎች መሆናቸውን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ያለውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እየቀረበ ስላለው ሰብአዊ ድጋፍ ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ተፈናቃዮች ካሉበት እጅግ አሳሳቢ የሰብአዊ ቀውስ አንጻር በቂ እንዳልሆነ፣ ልዩ ፍላጎት/ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያላማከለ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።
