የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ ቆጣሪዎችን እየቀየረ ነው።

በአሸናፊ አሰበ

ደምበኞች በቀላሉ አፕልኬሽኑን ሞባይላቸዉ ላይ በመጫን ያላቸዉን ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳብ በቀላሉ ለማወቅ፣ ከቆጣሪ ንባብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን  ለማስቀረት፣ የሃይል ስርቆትን ለመከላከል፣ የንባብ ስህተት ችግርን ለመቅረፍ እና ለመከላከል እንደሚያስችል የተነገረለት የዘመናዊ ቆጣሪ ቅየራ ስራ ሁለተኛ ዙር እንደተጀመረ  የፕሮጀክቱ ሃላፊ አቶ ጩመላ ሣሙኤል ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ትግበራ ሚያዚያ 2015 ዓም መጀመሩን እና በሙከራው ሂደት 5000 የስማርት ቆጣሪዎችን ማዳረስ መቻሉን የተናገሩት አቶ ሣሙኤል የፕሮጀክቱ ትግበራ በዋናነት የተጀመረው ከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ በሆኑ ወይም የሃይል ፍጆታቸው ከ 25 ኪሎ ዋት(KW) በላይ በሚጠቀሙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ላይ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ትግበራ 45 ሺህ ነባር ቆጣሪዎችን በ6 ወር ጊዜ ውስጥ በስማርት ቆጣሪዎች ለመቀየር ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
  
በሁለተኛው ዙር የሙከራ ፕሮጀክት ከታቀደው 45ሺ ቆጣሪዎች ውስጥ 14,000 ስማርት ቆጣሪዎችን ከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ለሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለማዳረስ መታቀዱን ሃላፊው ጨምረው ለአዲስ ጊዜ ገልጸዋል ።

እስካሁን በተሰራው የፕሮጀክት ሁለተኛ ዙር ትግበራ ስራ በአዲስ አበባ ከተማ 65፣ በአማራ 74፣ በሐረሪ 112፣ በደቡብ ምዕራብ 41፣ በሲዳማ 63፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 15፣ በድሬ ዳዋ 23፣ በሶማሌ 9፣ በጋምቤላ 10፣ በደቡብ 2፣ በአጠቃለይ 414 ነባር ቆጣሪዎች በስማርት ሜትር ተቀይረዋል ብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በሙከራ ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ በአነስተኛ ቁጥር መጀመሩን ያነሱት ሃላፊው ነገር ግን ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አኳያ ቀጣይነት እንደሚኖረው እና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደታቀደ የፕሮጀክት ሃላፊው አቶ ጩመላ ሳሙኤል ለአዲስ ጊዜ ገልጸዋል።