የአየር ንብረት ለውጥ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ

በዘላቂ የልማት ግቦች እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያጠነጥን የግማሽ ቀን አውደ-ጥናት ትናንት ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱን አዲስ ጊዜ አይታለች፡፡

ኤንዳ ኢትዮጵያ በመባል በሚታወቀው እና በዋናነት በከተማ ልማት እንዲሁም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ መርሀ-ግብር ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን በተለያዩ የዜና ማሰራጫ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሐን ባለሞያዎችም የውይይቱ አካል ነበሩ፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ምልክቶች እና እያስከተሉ ያሉት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በአውደ-ጥናቱ ላይ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በተለይ፣ ችግሩ ከኢትዮጵያ አንጻር የተዳሰሰበት ክፍል በተሳታፊዎች ዘንድ መነጋገሪያ እንደነበር መታዘብ ተችሏል፡፡ እ.አ.አ በ2030 ዓ.ም ይሳካሉ ተብለው ግብ የተያዘላቸው የዘላቂ ልማት ግቦች ምን እንደሆኑ እና ከቀረው ጊዜ አንፃር ያልተከወኑ የቤት ስራዎችን እንዴት እንወጣቸው በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያም ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡

የመርሀ-ግብሩን መጠናቀቅ ተከትሎ አስተያየታቸውን ለአዲስ ጊዜ የሰጡት የኤንዳ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ሀይማኖት ደሳለኝ “የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን የፈተነ እጅግ አሳሳቢ አደጋ ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም “በሀገር ደረጃ ለችግሩ ተገቢውን መፍትሔ ለመስጠት በቅድሚያ መንግስት በመቀጠልም የሲቪክ ማህበራት፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደየደረጃቸው ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል፡፡  

ኤንዳ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ እና በዘላቂ የልማት ግቦች ዙሪያ በቀጣይ በስፋት ለመስራት ማቀዱን አቶ ሀይማኖት ተናግረዋል፡፡