ኢትዮጵያ የአጎዋ እድልን ዳግመኛ እንድታገኝ መንግስት ሰላም ለማምጣት መስራት አለበት ተባለ፡፡


የሰሜን ኢትዮጵያዉን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ ከተጣሉት ማዕቀቦች ዉስጥ አንዱ የአጎዋ ነጻ የንግድ እድልን ማጣት ነው፡፡ እገዳው አሁንም አልተነሳም፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጎሹ ነጋሽ  እንደተናገሩት ፤ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፉ በእቀባዉ መጎዳቱን ተናግረዉ ኢትዮጵያ የአጎዋ እድልን ዳግመኛ እንድታገኝ ሰላም በማምጣት በኩል የቤት ስራዋን መስራት አለባት ብለዋል።

እግዱ ከተላለፈ በኋላ የታጣዉን የንግድ እድል ለማካካስ የተለያዩ ስራዎች በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሰራታቸዉን ያነሱት አቶ ጎሹ ፤ የገበያ ትስስርን መፍጠር ዋነኛዉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀላፊው ይህን ያሉት በኢትዮጵያ ባሉ የጨርቃጨርቅ አምራቾች የንግድ ትስስር ይፈጥራል የተብሎ የታመነበት አፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት ለ10ኛ ጊዜ በአዲስአበባ ስካይላይት ሆቴል ከጥቅምት 23- 26  እንደሚካሄድ በተገለጸበት ወቅት ነው፡፤

በመድረኩ የአፍሪካን የቆዳ ፣ ጨርቃጨርቅ ፣ አልባሳት እና የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ዉጤቶች ለእይታ ይቀርቡበታል። በባዛሩ ከ 25 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ከ 300 በላይ ላኪዎችንይሳተፋሉ፡፡

 ከ 6 ሺህ በላይ የሆኑ ጎብኚዎች እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ አቅራቢዎች እንደሚታደሙበት ተገልጿል።