“ሜታ በትግራይ ተወላጆች ላይ ለሚደርሰው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት አስተዋጽኦ አድርጓል” አምነስቲ ኢንተርናሽናል

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የትግራይ ተወላጆች ላይ በማነጣጠር ለተሰነዘሩ ማንነት ተኮር ጥቃቶች የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ ተባባሪ ሆኗል ሲል የአለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወቀሰ፡፡

አምነስቲ ትናንት ጥቅምት 20/2016 ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ “ሜታ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል” ያለ ሲሆን፤ ኩባንያው ጥላቻ እና ጥቃትን የሚያበረታቱ ይዘቶችን በበቂ ሁኔታ መቆጣጠርና መግታት አለመቻሉን ገልጿል፡፡

በዚህም “ፌስቡክ የሚከተለው ደካማ የንግድ ሞዴል እና መረጃዎችን የመቆጣጠር እንቅስቃሴ፤ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ እና የቅስቀሳ ዘመቻዎችን እንዳይቆጣጠር አድርጎታል” ያለ ሲሆን፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ወቅት በትግራይ ማህበረሰብ ላይ ለደረሰው ግፍ ኩባንያው የራሱን አስተዋፅዖ አድርጓል ብሏል፡፡

“የሞት ፍርድ አባቴ ላይ” በሚል ርዕስ የተጠናቀረው ይህ የአምነስቲ ሪፖርት 72 ገጾች ያሉት ሲሆን፤ ሪፖርቱ መነሻውን ፌስቡክ ላይ በተለጠፉ ቅስቀሳዎች አባቱ እንደተገደሉበት በተዘገበው አብርሃም ማዕረግ ታሪክ ላይ አድርጓል። ከዚህም በመነሳት ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለደረሱ የመብት ጥሰቶች ላይ ሜታ የነበረውን አስተዋፅዖን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በሪፖርቱ አካቷል፡፡

በዚህም ሜታ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊትም ሆነ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ከራሱ የፌስቡክ ተቆጣጣሪ ቦርድ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው እየተሰራጩ ስላሉ አደገኛ መልዕክቶች በርካታ ማስጠንቀቂያዎች ደርሰውታል ያለው አምነስቲ፤ ነገር ግን እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል እርምጃ ሲወስድ አለመታየቱን ገልጿል፡፡

አምነስቲ ፌስቡክ ላይ ከሚለጠፉ መልዕክቶች ጋር በተያያዘ የትግራይ ተወላጆች ላይ ደርሷል ያለው በደል፤ ከዚህ በፊት በሰሜን ምስራቅ እስያ በምትገኘው ማያንማር በዋናነት የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑ የሮሂንጃ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ከደረሰው እና ፌስቡክ አባብሶታል ከተባለው ጥቃት ጋር እንደሚመሳሰልም አመላክቷል።

ፌስ ቡክ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ዋነኛ እና ተዓማኒ የዜና ምንጭ ተደርጎ እንደሚወሰድ የጠቆመው ድርጅቱ፤ በዚህም የኩባንያው ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) በግጭቱ ወቅት በትግራይ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ጎጂ ይዘቶችን በማጉላት በአገሪቱ ለደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አስተዋፅዖ አድርጓል ሲል በሪፖርቱ ወቅሷል፡፡

“ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነው በትግራይ የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መአረግ አማረ በሕዳር ወር 2014 እንዲገደሉ አስተዋጽኦ ማድረጉ ነው” ያለው ድርጅቱ፤ በፕሮፌሰር መአረግ ላይ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ፌስቡክ ላይ ስለ መምህሩ መረጃዎች ሲዘዋወሩ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በዚህም ምክንያት ኩባንያው በሜታ ላይ የሚለጠፉ መልዕክቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋዎች በበቂ ሁኔታ ለማቃለል አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ሲል አምነስቲ አሳስቧል።

ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በሶማሊኛ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ቢሆንም፤ በቂ ተቆጣጣሪዎች የሉትም፣ የሚጠበቀውን ያህል ኢንቨስትመንት በይዘት ቁጥጥር ላይ አላደረገም የሚሉ ነቀፌታዎች በብዛት ይቀርቡበታል።

ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ ለደረሱ በደሎች አድርጎታል ከተባለው አስተዋፅዖ ጋር በተገናኘ ኹለት ክሶች በጎረቤት አገር ኬንያ ላይ የተመሰረተበት ሲሆን፤ ክሶቹም በግጭት አነሳሽ ይዘቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ የሚሆን 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እና ተጨማሪ 410 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ ደግሞ ፌስቡክ ስፖንሰር ባደረጋቸው ይዘቶች ለደረሱ ጉዳቶች የሚጠይቁ ናቸው።