1.5 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል የተባለ ስምምነት ተፈረመ::

ሰኞ ጥቅምት 19/2016

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሴቶችን እና ወጣቶችን አቅም በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል ያለውን የመግባቢያ ስምምነት ሄይፈር ኢንተርናሽናል ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ዛሬ ጥቅምት 19 2016 ዓ.ም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ከ ሄይፈር ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት ኤዲስዋ ኢፌዲ  ጋር የተፈራረሙ ሲሆን ከ 1 ሚሊየን እስከ 1.5 ሚሊየን ለሚጠጉ ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በአመት እስከ 3 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ሙፈርያት ባለፈው በጀት አመት 3.5 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አያይዘው ገልጸዋል ።

ሄይፈር ኢንተርናሽናል ከ 80 በላይ ሃገሮች የሚንቀሳቀስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከድርጅቱ ጋር በጋራ በመስራት በተለያዩ ክፍላተ አለማት ላይ ባለው ተደራሽነት ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል ተብሏል።

ስምምነቱ የዲጂታል ክህሎትን የማልማት ሥራ፣የፋይናንስ አቅም የመፍጠር እና የአቅም ግንባታ ሥራን የሚያካትት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ የስራ እድል ፈጠራውን ለማጠናከር የጀመርነውን እቅድ ያጠናክራል ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

በአሸናፊ አሰበ