ኬንያ የሁሉም የአፍሪካ አገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው።

ኬንያ የቪዛ ገደቦችን በማንሳት ሁሉም አፍሪካውያን ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ ግዛቷ መግባት እንዲችሉ በሯን ለመክፈት መዘጋጀቷን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ።

“አሁን የቪዛ ክልከላዎች አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩብን መሆኑን የተገነዘብንበት ወቅት ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ መናገራቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

ይህ ለአፍሪካውያን የቪዛ ጥያቄን ለማስቀረት የሚያስችለው የኬንያ ሃሳብ ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ፣ ማለትም በመጪዎቹ ሁለት ወራት ተግባራዊ እንደሚሆን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ገልጸዋል።

በአህጉሪቱ አገራት መካከል ከቪዛ ነጻ ጉዞ እንዲኖር ማድረግ ከአፍሪካ ኅብረት ያለፉት ዓመታት ግቦች አንዱ ነበር።በ2022 (እአአ) በወጣ አንድ ሪፖርት መሠረት ሲሸልስ፣ ጋምቢያ እና ቤኒን ብቻ ናቸው እስካሁን ለአህጉሪቱ ዜጎች ከቪዛ ነጻ ጉዞን የፈቀዱት።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በኮንጎ-ብራዛቪል ተገኝተው እንደተናገሩት ይህ የቪዛ ክልከላ ለአፍሪካውያን ሥራ እና ንግድ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።“ሰዎች ካልተንቀሳቀሱ የቢዝነስ ሰዎችም መንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህ ደግሞ ሁላችንም እንከስራለን” ብለዋል።

እንደ ኬንያ ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ማንኛውም አፍሪካዊ ኬንያን ለመጎብኘት ቪዛ አያስፈልገውም።ልጆቻችን አውሮፓ እንዳይገቡም ተደርገው አፍሪካ ውስጥም እንዳይንቀሳቁ መደረግ የለባቸውም።” ብለዋል።