ሰኞ ጥቅምት 19/2006
ካለፈዉ ሀምሌ ወር ጀምሮ በተፈጠረው የአማራ ክልል ግጭት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሁንም ከዕውቀት ገበታ ውጭ እንደሆኑ የተማሪ ወላጆች ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል ፡፡
በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደሚገኙ ያነሱነት ወላጆች በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ እንደወትሮውም ባይኾን መቀጠሉን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች እንዳሉ አንስተው አሁንም በቀጠለው የሰላም እጦት ምክንያት ልጆቻቸው በከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ላይ እንደሚገኙ ወላጆች ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለአዲስ ጊዜ የሰጡ በክልሉ የሚገኙ መምህራን በበኩላቸው የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እና ተማሪዎችን ወደ ዕውቀት ገበታቸው ለመመለስ መንግሥት፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ሰፊው ማህበረሰብ እንዲሁም ለጋሽ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ባለው ግጭትና በትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል ምክንያት በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደየሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መመለስ አልቻሉም።
ለዓለም አሰፋ
