ሰኞ ጥቅምት 19/2016
በ1995 ዓ.ም የወጣውን የብክለት ቁጥጥር አዋጅ 300/1995 አንቀጽ 20 መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው የተባለው እና በ 2011 ዓ.ም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የተላከው ደንብ እስካሁን አለመፅደቁን በኮሚሽኑ የአካባቢ ብክለት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉብርሃን ታሪኩ ለአዲስ ጊዜ ተናገሩ።
በ አዲስ አበባ የሚታየው ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን በድምጽ ማጉያ የታጀቡ የንግድ ማስታወቂያዎች፣ ሃይማኖታዊ መልዕክቶች፣ እና ከንግድ ቤቶች የሚለቀቁ ቅጥ ያጡ ሙዚቃዎችን መታዘብ ከጀመርን ዋል አደር ብሏል።
ይህንን የድምጽ ብክለት ለመከላከል ምን ተሰራ ስንል ከአዲስ ጊዜ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ብክለቱን ለመከላከል እንዲሁም አጥፊዎችን ለማስቀጣት ያግዛል ያልነውን ደንብ በእኛ በኩል አዘጋጅተን ብንልክም እስካሁን አልፀደቀም ብለዋል።ይህም ለስራችን ውጤታማ መሆን እንቅፋት ሁኖብናል ብለውናል።
ያም ሆኖ ከድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘ በሳለፍነው ዓመት እርምጃ የተወሰደባቸው ግለሰቦችና ተቋማት መኖራቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሯ ደንቡ እንዲፀድቅ ጠይቀዋል።
በአሸናፊ አሰበ
