ጥቅምት 19/2016
የሲዳማ ክልል መንግስት ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዙር 3ኛ የሤራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው፤ የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ 3 የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።
በዚህም መሠረት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕ/ሮ ፀጋዬ ቱኬ፣ ከሳቸው ጋር የዝምድና እና የጥቅም ትስስር እንዳላቸው የሚጠረጠሩት ተሰማ ደንጉሼ፣ እንዲሁም የቀድሞው የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮምሽነር የነበሩት አበራ አሬራ በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ምክንያት ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፏል።
ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከቀናት በፊት ወደ አገር ሲገቡ ቦሌ ኤርፖርት ላይ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው በሀዋሳ በሚገኝ የእስረኞች ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ የክልሉ ፖሊስ ማሳወቁ አይዘነጋም።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በክልሉ አራት ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ በቀረበለት ሞሽን ላይ ተወያይቶ አፅድቋል። የፍርድ ቤቶቹ መቀመጫም በአለታወንዶ፣ በበንሳ፣ ይርጋለምና ሀዋሳ ከተሞች ላይ እንዲሆን ወስኗል።
የምክር ቤቱ ሌላኛው አጀንዳ የአመራሮች ሹመት መስጠት አንዱ ሲሆን፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የሦስት ሥራ ሀላፊዎች ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በዚህም መሰረት ጎሳዬ ጎዳና የክልሉ ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣ ሰላማዊት መኩሪያ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣ ወሰንየለህ ስምኦን የክልሉ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ሆነው እንዲመሩ ተሹመዋል
