የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል ተባለ።

ሰኞ ጥቅምት 19/2016

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ባሰራጨው ዘለግ ያለ ዘገባ ከ ሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ ባሉት ጊዜያት በአማራ  ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎች ወይም ወረዳዎች በአንድ ወቅት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ በሌላ ወቅት በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) ቁጥጥር ሥር ውለዋል። የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ሲል ገልጿል።

በግጭቱ ዐውድ የአየር/ድሮን መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት የተነሳ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል ያለው ዘገባው ሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ፣ መጥተህ ብላ ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ደግሞ ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ፣ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል ሲል አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል ያለ ሲሆን  በምንጃር ወረዳ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀያቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3000 የሚሆኑት አሞራ ቤቴ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሃራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል ብሏል።

በተለይም በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ ይገኛል ያለ ሲሆን ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ” በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል ብሏል።

እንደማሳያ በባሕር ዳር ከተማ፣ ሰባታሚት አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ አዴት ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ሰዎች፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ አማኑኤል ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ለመረዳት ተችሏል። እንዲሁም በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ ግንደወይን ከተማ ሞጣ በር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በጥይት የቆሰለን ግለሰብ እናቱና እህቱ በባጃጅ አሳፍረው ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ላይ እያሉ፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባጃጁን አስቁመው ሁሉንም ተሳፋሪዎች ካስወረዱ በኋላ “የቆሰለው እኛን ሲዋጋ ነው” በሚል ምክንያት የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራቱን ሰዎች በጥይት እንደገደሏቸው ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል….

ተጨማሪ ያንብቡ
https://ehrc.org/?p=25435