ከንቲባ አዳነች አቤቤ የክብር ዶክትሬት ተበረከተላቸው::

አሜሪካ ጆርጂያ ግዛት የሚገኘው ትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደርስ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት እንዳበረከተላቸው ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታወቁ።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር እና የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለሌሎች ሃገራት መሪዎች አርአያ የሚሆን ስራ በመስራታቸው የጆርጂያ ግዛት የክብር ዜግነት ሽልማት እንደተበረከተላቸው የግዛቱ ሴናተር ጋይል ዴቨንፓርት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል ተብሏል::

ከንቲባዋ ለተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እና የጆርጂያ ግዛት ላበረከተልኝ የክብር ዜግነት አዋርድ እንዲሁም የአትላንታ ከንቲባ አንድሬ ዲከንስ ላደረጉልኝ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ ብለዋል።

በተጨማሪም ከከንቲባ አንድሬ ዲከንስ ጋር በነበረን ቆይታ የሁለቱን ከተሞች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ በሚያስችሉ መንገዶች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ሲሉም በገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል።