የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክቱን ወደ ሽሬ ለማድረግ የጀመረው እንቅስቃሴ ተቃውሞ ገጠመው

ጥቅምት 12/2016

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጎንደር ዲስትሪክት የነበረውን ወደ ትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ለማዞር የጀመረው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጿል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ውስጥ ሲሰጠው የነበረው አገልግሎት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቶ ነበር ብለዋል፡፡

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ዲስትሪክቱን ጎንደር በማድረግ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ሆኖም፣ በአሁኑ ሰዓት በተቋሙ የተዘረጋው ሥርዓት ስራ ሊያጓትት የሚችልና በህዝብ ዘንድ ቅሬታን የሚያስነሳ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ወቅሰዋል፡፡

በአራቱም የአገልግሎት ማእከላት ማለትም ዳንሻ፣ ባህከር፣ አድረመጥ እና ሁመራ የሚገኙ የባለሙያዎችን ደሞዝ ጭምር ወደ ሽሬ ዲስትሪክት በማዛወር በሽሬ በኩል እንዲሰጣቸው እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል በቀደመው ይቀጥል በሚል አገልግሎቱን ወደ ትግራይ ለማሻገር መሞከር የአገልግሎት አሰጣጡን ከማወሳሰቡም በላይ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከጎንደር ዲስትሪክት የተዘረጋውን ሲስተም በተሟላ መልኩ በማስጀመር እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መናኸሪያ ራዲዮ ስለጉዳዩ ጠይቄያቸው ነበር ያላቸው አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ባለሙያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፌደራል ተቋም እንጂ የፖለቲካ ተቋም አይደለም ብለውኛል ብሏል፡፡

በተጨማሪም ለሕዝብ አገልግሎቱን መስጠት እንጂ ዲስትሪክቱን የፈለገበት ቦታ ማድረግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አዲስ ጊዜ የዜና መሰረታዊ መርሆዎችን ያልጣሱ  የሐገር ውስጥ፣የአፍሪካ ቀንድ እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን የሚያስነብብ የዜና ገፅ ነው።