ጥቅምት 12/2016
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት እና አለመረጋጋት በነበረበት ወቅት 23 የወርቅ እና የከበሩ ማዕድናት ሳንቲሞች መጥፋታቸው እንደተረጋገጠ የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ገ/መድህን ፍፁም ብርሀን ለአዲስ ጊዜ ገለፁ፡፡
አክሱም ከተማ በቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተች ከተማ መሆኗን የገለፁት ሀላፊው በጦርነቱ ከወደሙት ቅርሶች ባለፈ የተዘረፉና የጠፉ 23 የወርቅ እና የከበሩ ማዕድናት ሳንቲሞች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሀላፊው ጨምረው፣ የነዚህ ቅርሶች መጥፋት በከተማዋ የቱሪዝም እንቀስቃሴ ላይ ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አብራርተዋል፡፡
የጠፉትን ቅርሶች ማን እንደወሰዳቸው ማወቅ እንዳልተቻለ የገለፁት ሀላፊው እነዚህን ቅርሶች የማስመለስ ስራ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ገ/መድህን ፍፁም ብርሀን እንደገለጹልን፣ ጽሕፈት ቤታቸው በዋናነት እየሰራ ያለው ከፌደራል እና ከክልል ፖሊሶች ጋር በጥምረት በመሆን ቅርሶቹ ሀገር ውስጥ ካሉ ከሀገር እንዳይወጡ የማድረግ ስራ ነው፡፡
ሀላፊው በማጠቃለያቸው ላይ ቅርሶቹን የማስመለስ ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስምረውበታል፡፡
አዲስ ጊዜ የዜና መሰረታዊ መርሆዎችን ያልጣሱ የሐገር ውስጥ፣የአፍሪካ ቀንድ እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን የሚያስነብብ የዜና ገፅ ነው። ለበለጠ መረጃ እዚህ ይጫኑ
