ዳግም የተስፋፋውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነ

ጥቅምት 12/2016
በጣና ሀይቅና በዙሪያው በድጋሚ የተስፋፋውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው የጣና ሀይቅ እና ሌሎች ውሀማ አካላት ኤጀንሲ ገልጿል።
ሀሳባቸውን ለአዲስ ጊዜ የሰጡት የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ መልካሙ አዳም በበኩላቸው አረሙ መስፉፉቱን መመልከታቸዉን አንስተው ከዚህ ቀደም ችግሩን ለመከላከል ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል።
የጣና ሀይቅ እና ሌሎች ዉሀማ አካላት ኤጀንሲ ሀላፊው አቶ ፈንቴ አለም የእምቦጭ አረሙ ምን ያህል ሄክታር እንደተስፋፋ መረጃዉ እንደሌላቸው አንስተው ባለው የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ችግሩን ለመቅረፍ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የባሕር ዳር ነዋሪዎች እንደነገሩን እየተስፋፋ የመጣው አረም በአፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው የሀይቁ ቱሪዝም ላይ እክል እንዳይሆን ስጋት እንዳደረባቸው አንስተዋል።
እንደከዚህ ቀደሙ የሰው ጉልበት በመጠቀም እንቦጬን ለማስወገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ያነሱት ነዋሪዎቹ የፀጥታው ችግር እና የመንግስት ቸልተኝነት ተቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
በ2004 ዓ.ም መከሰቱ የተነገረለት የእንቦጭ አረም አሁንም ከሀይቁ ላይ ማጥፋት ባለመቻሉ የሐይቁ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደጣለ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።
አዲስ ጊዜ የዜና መሰረታዊ መርሆዎችን ያልጣሱ የሐገር ውስጥ፣የአፍሪካ ቀንድ እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን የሚያስነብብ የዜና ገፅ ነው። ለበለጠ መረጃ እዚህ ይጫኑ