ሰኞ ጥቅምት 12/2016
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ አዲስ ባወጣው የሩብ ዓመት ሁኔታዊ ሪፖርት በኢትዮጵያ 8 ሺህ 552 ያህል ትምህርት ቤቶች በሙሉ እና በከፊል ዝግ መሆናቸውን ገልጿል። በዚህም 7 ነጥብ 6 ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጨ መሆናቸውን አስታውቋል።
የትምህርት ቤቶቹ መዘጋትም ሆነ የህጻናቱ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ችግር መሆኑን የጠቆመው የዩኒሴፍ ሪፖርት በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት ለችግሩ መስፋፋት በቀዳሚነት የተቀመጠ ምክንያት ሆኗል።
በዩኒሴፍ የተቀመጠው በሙሉ እና በከፊል የተዘጉ ትምህርት ቤቶች አሀዝ ሀያ በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እንደሚሸፍን ሪፖርቱ በማብራሪያው ላይ አስቀምጧል።
ድርጅቱ በማጠቃለያው ላይ ጊዜው በተራዘመ እና ህጻናቱ በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ካልተደረገ መጪው ጊዜ የከፋ ይሆናል ሲልም አሳስቧል።
አዲስ ጊዜ የዜና መሰረታዊ መርሆዎችን ያልጣሱ የሐገር ውስጥ፣የአፍሪካ ቀንድ እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን የሚያስነብብ የዜና ገፅ ነው። ለበለጠ መረጃ እዚህ ይጫኑ
