ጥቅምት 10/2016
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች በታጣቂዎች እንደታገቱ የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡
አጋቾቹ የያዟቸውን ሰዎች ለመልቀቅ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቁ የተነገረ ሲኾን ከድርጊቱ መደጋገም የተነሣ ከፍተኛ ስጋት እንደገባቸው የገለጹ ነዋሪዎችም ቀዬአቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
እገታ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአንዳቸው እንደተወለዱ የሚናገሩትና ስለኹኔታው እንደሚያውቁ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ፣ ሰሞኑን ስምንት አርሶ አደሮች በነፍስ ወከፍ እስከ 300ሺሕ ብር የማስለቀቂያ ዋስትና እንደከፈሉ ተናግረዋል፡፡ ከእገታው የተለቀቁ አንድ ግለሰብ ደግሞ፣ ነጻ ለመውጣት ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋራ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ከፍለናል ሲሉ ለዜና ማሰራጫዎች ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ኃይሉ አዱኛ፣ መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለውንና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ለእገታው ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ እንደኾኑ የሚገልጹት አቶ ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው ውንጀላውን ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
