ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ትናንት ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ለማቀርበው የምግብ እርዳታ የአማራ ክልል ግጭት እና የገንዘብ እጥረት ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብኛል ሲል አስታወቀ።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል በዘጠኝ ዞኖች በአሁኑ ወቅት በትጥቅ የተደገፈ ከፍተኛ ግጭት በመኖሩ እንቅስቃሴው መገደቡን እና በክልሉ የሚገኙ ሰራተኞቹን ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ንብረቶቹ እንዳይዘረፉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በተጨማሪም፣ እስከ አመቱ አጋማሽ ድረስ የረድኤት አቅርቦቱን በአግባቡ ለማከናወን ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 219 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እጥረት እንደገጠመው የገለጸው ድርጅቱ በዚህም ሳቢያ በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ 50 በመቶ ለሚሆኑት ብቻ ለማቅረብ መገደዱን ጠቁሟል።
እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ እርዳታን የሚጠባበቁ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሚሊየን እንደሚበልጥ እና ከነዚህ ውስጥም 11 ሚሊየን የሚሆኑት የምግብ ችግር ያለባቸው፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ወደ ቀያቸው የተመለሱ እንደሚገኙበት እንዲሁምየመንግስታቱ ድርጅት የረድኤት ተቋምን ጨምሮ ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው አቅርቦቱ የሚሟላላቸው መሆኑን አመላክቷል።
