በክልሉ የቀጠለው ግጭት ፈተና እንደሆነባቸው የአማራ ተማሪዎች ገለጹ

ጥቅምት 10/2016

በአማራ ክልል ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ በመጣው ግጭት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት በመስተጓጎሉ በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደየሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መመለስ እንዳልቻሉ ተናገሩ፡፡

በሲዳማ ክልል በሚገኘው ሀዋሳ እንዲሁም በዲላ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ የገለጹት ተማሪዎች፣ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባም ኾነ የአውሮፕላን በረራ ወዳለባቸው ከተሞች ለመሔድ እንደተቸገሩ ለቪኦኤ የዜና ማሰራጫ ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ተማሪዎች ደግሞ፣ ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ የየብስ ትራንስፖርት ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ሦስት እጥፍ በኾነ ወጪ ከአካባቢዎቹ በአውሮፕላን ለመውጣት እንደተገደዱ ጠቅሰው፣ መንግሥት ወደየሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያደርሳቸው ጠይቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮች በበኩላቸው፣ የዐማራ ክልል ተማሪዎቻቸውን በከፊል እየተቀበሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ፣ “ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው፤ ድጋፍ እና ክትትልም እያደረግኩ ነው” ብሏል፡፡