መከላከያ በ“ሸኔ ቡድን” ላይ ወሰድኩት ባለው እርምጃ ዋና አመራሩን ገድያለሁ አለ

Ethiopian army

ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም  

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት “ሸኔ” ብሎ በሚጠራው ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ላይ በወሰደው እርምጃ የቡድኑ ከፍተኛ አመራር የሆነው ጃል ቦሩ አምቦን እና ሌሎች በርካታ የቡድኑ አባላትን መግደሉን አስታወቀ።

መከላከያ ሰራዊቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባሰፈረው ሀተታ በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አባላት በምዕራብ ሽዋ ዞን በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ፋጅና ጌርጌራ በተባሉ አካባቢዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረው ታጣቂ ቡድንን መደምሰሱን አስታውቋል።

መከላከያ በዚህ መግለጫው ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን እና ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሻምበል እንግዳሸት መከተን ጠቅሶ መረጃውን አስፍሯል።

በተመሳሳይ በጀልዱ ወረዳ በጩልቄ እና በሽኩቴ አካባቢዎች ላይ ቡድኑ በሰነዘረው የማጥቃት ሙከራ እቅዱ እንዳልተሳካ በመግለፅ ሰራዊቱ የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በማክሸፍ እንዲመለስ ማድረጉን ሻምበል ከረሚላ ሙሃመድ መግለጻቸውን አስታውቋል። በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ትላንት ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም የኢስት ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞች የሆኑ የቻይና ዜጎችን አግተው መውሰዳቸውን አዲስ ስታንዳርድ የተባለው ድረገጽ መዘገቡ ይታወሳል።