ሥራ አጥነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ችግር እንደሆነ መንግሥት አመነ

ቅዳሜ ጥቅምት 10/2016

በኢትዮጵያ፣ ሥራ አጥነት እጅግ አሳሳቢ ብሔራዊ ችግር ከኾነበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በአዲስ አበባ የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የሥራ ዐውደ ርእይ ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር፣ ሥራ አጥነት የችግሮች ሁሉ አውራ እንደኾነ ገልጸው፣ መፍትሔው የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

ባሳለፍነው ረቡዕ የተከፈተው ዐውደ ርእይ፣ ከ20ሺሕ በላይ አዲስ ተመራቂ ሥራ ፈላጊዎችንና 200 ቀጣሪ ድርጅቶችን እንደሚያገናኝ ተነግሮለታል። ልዩ ልዩ አካላት በትብብር እንዳዘጋጁት የተነገረለት ይኸው ሀገር አቀፍ የሥራ ዐውደ ርእይ፣ ለስድስት ሺሕ አዲስ ተመራቂዎች፣ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል፡፡ በዝግጅቱ የተሳተፈው ዳሽን ባንክ፣ በሁለት ቀኑ የሥራ ዐውደ ርእይ፣ ሦስት ሺሕ አዲስ ምሩቃንን እንደሚቀጥር አስታውቋል፡፡

 ዐውደ ርእዩ፣ ተቀጣሪዎችንና ቀጣሪዎችን በማገናኘት መልካም ዕድል እንደፈጠረ፣ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች እና ሥራ ፈላጊዎች         ተናግረዋል ሲል ቪኦኤ የዜና ማሰራጫ ዘግቧል።

እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር፣ በ2050 በኢትዮጵያ ለሥራ ብቁ የሚሆነው ዜጋ ቁጥር ወደ 188 ሚሊዮን እንደሚያድግ ትንበያዎች የሚያሳዩ ሲሆን በየዓመቱ ባለው ከፍተኛ የሥራአጥ ቁጥር ላይ፣ ሌሎች ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ስራ ፈላጊዎች የሥራ ገበያውን እየተቀላቀሉ መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚንስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በወቅቱ ከዶቼ ቬሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል።