ቅዳሜ ጥቅምት 10/2016
በጎረቤት ሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ያለመ እና የሱዳን ሲቪል ተቋማት የሚሳተፉበት ጉባዔ ከዛሬ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚያካሄድ ተገለጸ።
የሱዳን ሲቪል ሀይሎች በአዲስ አበባ በሚያካሂዱት በዚህ ጉባዔ ዋነኛ ትኩረት የሚሆነው በሀገሪቱ ለስድስት ወራት የዘለቀውን ግጭት እልባት ለመስጠት የሚያስችል ስልት መቀየስ መሆኑን ታማዙጂ ራዲዮ በድረገጹ ላይ በሰራው ዘገባ ጠቁሟል።
በሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጉባዔ ለማሳለጥ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ከተሳታፊዎች አንዱ የሆነው ኡማ ፓርቲ የሚዲያ ሃላፊ ሚስባህ አህመድ መሃመድ አረጋግጠዋል።
ጉባዔው ከ70 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የሱዳን ሲቪል ተቋማትን እና ማህበረሰብ አንቂዎችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
የጉባዔው ዋነኛ ግብ በቀጣይ ወር መጀመሪያ ለሚካሄደው ሁሉን አቀፍ አጠቃላይ ኮንፈረንስ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እና ዝግጅቶችን ማድረግ መሆኑን የኡማ ብሔራዊ ፓርቲ የሚዲያ ሃላፊው ሚስባህ አህመድ መሃመድ ገልጸዋል። በኮንፈረንሱ የሀገሪቱን የእርስ በርስ ግጭት በማስቆም የጋራ የፖለቲካ ራዕይ እንዲኖር የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ የዲሞክራሲ ሂደቱን ማስጀመር መሆኑንም አመላክተዋል።
