ሐሙስ 08/2016
በሀዲያ ዞን በምትገኘው ሾኔ ከተማ ውስጥ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ስራ ማቋረጡን ከአካባቢው የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ላለፉት ሶስት ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም ያሉ ሰራተኞች ባነሱት የስራ ማቆም አድማ መነሻነት መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ተድላ አካሉ በሾኔ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል ስራ ማቆሙን አምነው አገልግሎት መስጠት ካቆመ አንድ ሳምንት ማስቆጠሩን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
ይህን የዶክተር ተድላ ሀሳብ የተጋሩት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ተሰማ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ግን እንደተቆጠቡ ቪኦኤ የዜና ማሰራጫ በዘገባው አብራርቷል፡፡
ይህ አጋጣሚ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ የሚናገሩትና በባለሞያነት ሲያገለግሉ የቆዩት የተቋሙ ሰራተኞች፣ ከዚህ ቀደም የበጀት እጥረትን ምክንያት በማድረግ በተፈጠሩ የክፍያ መስተጓጎሎች በርካታ ሰራተኞች ከስራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሚሰሩ በአጠቃላይ ከ500 በላይ የሆስፒታሉ ሰራተኞች በተሳተፉበት በዚህ የስራ ማቆም አድማ ለ600ሺ ህዝብ የህክምና አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ስራ አቁሟል፡፡
