ሐሙስ ጥቅምት 08/2016
ካለፈው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል እየሰፋ የመጣው ግጭት በተለይ በጎጃም አንዳንድ አካባቢዎች አሁንም መቀጠሉን አዲስ ጊዜ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
አንፃራዊ ሰላም ካለባቸው ከተሞች ውጭ በመከላከያ ሰራዊቱ እና በፋኖ ታጣቂ ቡድን መካከል ያለው ግጭት አሁንም በበርካታ የገጠር ቀበሌዎች መኖሩን እኚሁ ነዋሪዎች አረጋግጠውልናል፡፡ ሰዓት እየጠበቁ የሚሰሙት የከባድ መሳሪያ የተኩስ ድምፆች የረጋ ሕይወት እንዳይኖራቸው ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ምስክርነታቸውን ለአዲስ ጊዜ የሰጡት፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ “ቡሬ ከተማ ላይ ጊዜያዊ ሰላም ቢኖርም ትናንት ከከተማው በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኝ ሸንዲ ከተማ አጠገብ ካለው ሰባ አዳር የሚባል አካባቢ ዙርያ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ይሰማ ነበር” ሲሉ በመግለፅ ችግሩ ተባብሶ ወደ ከተማው እንዳይመጣ በሚል ስጋት ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ በመምህርነት ስራ ላይ የተሰማሩትና ስለክስትቱ የጠየቅናቸው ሌላኛው ምስክርም የግጭቱን መቀጠል አረጋግጠውልናል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያስተናገደች የምትገኘው የምስራቅ ጎጃም ዞን ከተማዋ ደብረ ማርቆስ አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም እንደሰፈነባት ነዋሪዎቹ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።
በከተማዋ ከሶስት ቀናት ወዲህ የስልክ እና አንዳንድ ማህበራዊ አገልግሎቶች መስራት እንደጀመሩ የገለጹልን ነዋሪዎች ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች በቅርብ ርቀት ተፋጠው መገኘታቸው ግን የስጋት ምንጭ እንደሆነባቸው አልሸሸጉም።
በአቶ አረጋ ከፋለ የሚመራው የክልሉ መስተዳድር አመራር በቅርቡ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው።
