የ12ኛ ክፍል ውጤት እኛንም አስገርሞናል-ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

Ethiopian education minister

ጥቅምት 07/2016

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ዶር) ዛሬ በርላማ ተገኝተው ከሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለሚኒስትሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን የሚመለከተው ይገኝበታል።

የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያሰሙት የፓርላማ አባል “በተከታታይ ለሁለት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት በጣም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ትምህርት ሚኒስቴር የፈተናውን ውጤት እንዴት ያየዋል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ፕ/ር ብርሃኑ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “የ12ኛ ክፍል ውጤት እንደዚህ መሆን ሁላችንንም አስገርሞናል” ብለዋል።

“የፈተናውን አሰጣጥ መቀየር ብቻ ይሄን ካሳየ፤ ከዚህ ተነስተን ብቸኛ ነገር ልንል የምንችለው፤ ከዚያ በፊት ስንሰጣቸው የነበሩ ፈተናዎች በሙሉ የተማሪን እውነተኛ ችሎታ የሚያሳዩ አይደሉም ማለት ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ይሰጡ በነበሩ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በትምህርት ቤቶች እና በክልል ደረጃ ሳይቀር በተደራጀ መልኩ “ፈተናዎች የሚሰረቁበት” እንደነበር የጠቀሱት ፕ/ር ብርሃኑ፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ውጤቶች የተማሪዎችን ችሎታ የሚያንጸባርቁ እንዳልነበር አስረድተዋል።

“የዘንድሮ ፈተናለመጀመሪያ ጊዜ እውነታውን አድርጎልናል። አሁን የምንደበቅበት ቦታ የለም። ሰርቀን የምናሳይበት ቦታ የለም። ራቁታችንን ምን እንደምንመስል አይተነዋል” ሲሉም የትምህርት ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።