የሰላም እጦት ለሱሰኛ ቁጥር መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ተባለ

addiction

ጥቅምት 07/2016

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰላም እጦት እና የስራ አጥነት ቁጥር መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ለመጣው የሱስ ተጠቂዎች ቁጥር ሚናው የጎላ እንደሆነ በአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት አስራት ጫካ ለአዲስ ጊዜተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሚሊዮኖች መፈናቀል እና ሞት ምክንያት ሲሆን፣ ቁጥራቸው የማይገመት ህጻናትንም ቤተሰብ አልባ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ከ 5.5 ሚሊየን የሚልቁ ህጻናት ወላጅ አልባ እንደሆኑ የዩኒሴፍ ዘገባ የሚያመላክት ሲሆን ይህም ህጻናቱን ለሱስ የሚኖራቸውን ተጋላጭነት ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል።

ጦርነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል እና ድርቅ ለሱስ አጋላጭነት ቀላል የማይባል ሚና እንደሚጫወቱ ሱስ ላይ የተሰሩ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሰፊ ሽፋን ያለው ሱስ አምጪ ንጥረ ነገር የአልኮል መጠጦች ሲሆኑ ጫት እና ሲጋራ ቀጣዩን ደረጃ ይይዛሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ 2016 በተካሄደው የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብ እና ጤና ዳሰሳ (EDHS) ጥናት እንደሚያመለክተው  35 በመቶ ሴቶች እና 46 በመቶ ወንዶች በህይወታቸው በአንድ  ወቅት ለአልኮል መጠጦች ተጋላጭ ሆነው እንደሚያውቁ አመላክቷል፡፡

እንዲሁም ሰላሳ በመቶ የሚሆኑ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና በዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ወጣቶች ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮችን እንደሚጠቀሙ ዘገባዎች ያትታሉ፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከለከሉ አደንዛዥ እጾች እና ከታለመለት አላማ ውጭ አገልግሎት ላይ በሚውሉ መድሃኒቶች ምክንያት የሱሰኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ሲሆን “በትራማዶል እና ፔቲዲን በተሰኙ መድኃኒቶች ምክንያት ለሱስ የሚጋለጡ ወጣቶች እና የህክምና ባለሞያዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” ሲሉ አቶ አስራት አክለዋል።

ሱስ እና ለሱስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መፍትሄው ምንድነው ስትል አዲስ ጊዜ የጠየቀቻቸው አቶ አስራት ‹‹ሱስ የአዕምሮ ህመም መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር፣ ለሱስ የተጋለጡ ሰዎች የሚያሳዩዋቸውን ምልክቶችን ደግሞ መለየት ይገባል ብለዋል። ትምህርት ቤቶችን ተጠግተው የተሰሩ የአልኮል ንግድ ቤቶች እና የማጨሻ ቤቶች ከትምህርት ተቋማት አካባቢ እንዲርቁ ጠንከር ያለ እርምጃ እናዲወሰድ ቢደረግ እንዲሁም ለሱስ መበራከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘውን የህጻናት ወደ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሰት የሚገታበት መንገድ ቢፈለግ በየመንገዱ ከምንመለከታቸው ማስቲሽ የመሳብ ሱስ ከመቀነስ አኳያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል›› ሲሉ መክረዋል።

ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት በሚመለሱበት ጊዜ የልጆቻቸውን ቦርሳ መመልከት እና የጠረን ለውጦች ካሉ መፈተሸ እንደሚገባቸው አቶ አስራት ገልጸው ከሱስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ እምቢተኝነት፣ ተቃራኒ እና በቀላሉ አኩራፊ መሆን እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር አለመስማማት የመሳሰሉት ምልክቶች ሲታዩ ችላ ማለት እንደሌለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲ የሚቀርጹ አካላትም ለአዕምሮ ህክምና ትኩረት እንዲሰጡ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡