ከሱዳን 38ሺህ ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለፀ

sudan

ጥቅምት 07/2016

በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎችን ግጭት በመሸሽ 38ሺህ 560 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን አለምዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ፡፡

ስድስተኛ ወሩን ከተሻገረው እጅግ ደም አፋሳሽ ከሆነው ከዚህ ጦርነት ራሳቸውን ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ አጠቃላይ ስደተኞች ቁጥር 85ሺህ 600 መሻገሩን ድርጅቱ ያወጣው ዝርዝር መግለጫ ያመለክታል፡፡ ከዚህ መካከል 30ሺህ 560 ያህሉ ኢትዮጵያን ሲሆኑ 31ሺህ 115 የሚሆኑት ደግሞ ሱዳናውያን ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡ የተቀሩት 15ሺህ 821ዱ ደግሞ የሶስተኛ ሀገራት ዜጎች ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ወደ ሌሎች ሀገራት መሻገራቸውን የፍልሰተኞች ድርጅት መረጃ ጠቁሟል::

አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት ከ85ሺህ በላይ ስደተኞች መካከል 35ሺህ 440 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ 50ሺህ 56 ያህሉ ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡

በዚህ ጦርነት ምክንያት እስከአሁን 1.2 ሚሊየን ያህል ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንደተሰደዱ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ስደተኞችን በመቀበል ቻድ ቀዳማዊ ስትሆን ግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ መካከለኛዋ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሊቢያም ብዛት ያላቸው ስደተኞችን የተቀበሉ ሀገራት ናቸው፡፡