ጥቅምት 07/2016
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ታምሩ ገምበታን ጨምሮ በቁጥር ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ተሰማ።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰሞኑን ሲሆን አቶ ታምሩ ገምበታ ግን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ተገልጿል።
የምክትል ዳይሬክተሩ ቤት በፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መፈተሹንና ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ ከተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ እንዳሉ ይታወቃል።
አገልግሎቱን በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፣ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ፍራኦል ጣፋና አቶ ታምሩ ገምበታን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከ3 ወራት በፊት ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ተቋሙ ከፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል።
በተጨማሪ ከዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በሕወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር ሲልኩ ነበር የተባሉ 16 የተቋሙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም 5 በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በተያዘው ሳምንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተሰማው ምክትል ዳይሬክተሩን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም ከሙስና ጋር በተያያዘ መጠርጠራቸው ተገልጿል፡፡
