ጥቅምት 07/2016 (ቀይ ባሕር)
ከሱማሊላንድ በመነጠል ከሀገረ ሶማሊያ ጋር አንድነት ለመፍጠር እየታገለ ያለው የአውዳል ግዛት ንቅናቄ፣ ኢትዮጵያ በዘይላ ወደብ በኩል ወደ ቀይ ባህር ለመቅረብ ፍላጎት ካላት ሙሉ ትብብር እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡ ንቅናቅው ትናንት ባወጣው ዝርዝር መግለጫ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ የሰጡትን ማብራርያ እንዳጤነው ዘርዝሮ “ይህን ህልማቸውን ለማሳካት በይፋ ግብዣ አቀርባለው” ሲል የጠቅላይ ሚንስትሩ ሀሳብ ተጋሪ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የአውዳል ግዛት ንቅናቄ፣ ታሪካዊው የዘይላ ወደብ ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ክፍት እንደሚሆን እና ይህም በመግባቢያ ሰነድ እንደሚፀና በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርል፡፡ ጨምሮም ይህ ሂደት ሁሉንም ወገን አሸናፊ ያደርጋል ሲል ደምድሟል፡፡
ይህ የአውዳል ግዛት ንቅናቄ መግለጫ በሶማሊያውያን ዘንድ መነጋገርያ እየሆነ እንዳለ የአዲስ ጊዜ የዜና ክፍል ባደረገው ዳሰሳ የተረዳ ሲሆን በርካቶች የህዝብ ውይይት ያልተካሄደበት የተናጥል ውሳኔ ሲሉ የንቅናቄውን መግለጫ አጣጥለውታል፡፡
