ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ እና የቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል ሆስፒታል ላይ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ

paulos hospital

በ-እታገኘሁ መኮነን

በተደጋገሚ የህክምና ስህተት አራት ጊዜ ቀዶ ህክምና ለማድረግ የተገደዱት እና ሁለት ጊዜ ባዕድ ነገር የሰውነት ክፍላቸው ውስጥ የተረሳባቸው ግለሰብ የሁለት ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ አገኙ፡፡

ግለሰቡ አቶ አስማረ አለሙ ይባላሉ፡፡ የኢሊባቦር በደሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ 2006 ላይ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው በአንድ አንጋፋ ሆስፒታል የሀሞት ጠጠር እንዳለባቸው እና ቀዶ ህክምና እንደሚደረግላቸው ይነገራቸዋል፡፡ አቶ አስማረ ቀዶ ህክምናውን አጠናቅቀው ወደ በደሌ ቢመለሱም ህመሙ ስለበረታባቸው ተመልሰው መጥተው ምርመራ ቢያደርጉም ምንም የጤና ችግር እንደሌለባቸው በመንገር ይመልሷቸዋል፡፡

ሆኖም ሌላ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ምርመራ ሲያደርጉ የሰውነት ክፍላቸው ውስጥ ካቲተር እንዳለ ይነገራቸዋል፡፡ እናም ወደ ሌላ አንጋፋ ሆስፒታል በመሄድ ቀዶ ህክምና በማድረግ ካቲተሩ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ያም ሆኖ የአቶ አስማረ ጤና አልተመለሰም፡፡ ወደ ሆስፒታሉ ተመልሰው መጥተው ሲታዩ እዚኛው ሆስፒታል ደግሞ በቀዶ ህክምናው ወቅት ካቲተሩ ወጥቶ  ጎዝ ወይም ጨርቅ ተረስቶ እንደተሰፋ ይነገራቸው እና ለሶስተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና ያደርጋሉ፡፡ ጨርቁ እንደወጣም ይነገራቸዋል፡፡

አሁንም ግለሰቡ በተለይ ኩላሊታቸው አካባቢ ተደጋጋሚ ህመም ያሰቃያቸዋል፡፡ ከበደሌ ወደ ጅማ ሄደው ተጨማሪ ምርመራ ሲያደርጉ በቀዶ ህክምናው ወጥቷል የተባለው ጨርቅ እንዳልወጣ እና በድጋሚ ለአራተኛ ጊዜ ቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማሉ፡፡ እናም በጅማ ሪፈራል ሆስፒታል ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸው የተረሳው ጨርቅ ይወጣላቸዋል፡፡ እንደዚህ አይነቱ ታሪክ ያጋጠማቸው ግለሰብ ሁለቱ ሆስፒታሎች ላይ የህክምና ስህተት ፈጽመውብኛል ብለው ክስ መሰረቱ፡፡ አራት አመታትን የፈጀው የክስ ሂደትም ባለፈው አርብ መስከረም 30፣ 2016 እልባት አገኘ፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት በግለሰቡ ላይ እንዲህ አይነቱን በደል ያደረሱት ሁለቱ ሆስፒታሎች ማለትም ደጃዝማች ባልቻ ሪፈራል ሆስፒታል እና ቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል ሆስፒታል እያንዳንዳቸው ለግለሰቡ አንድ አንድ ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ እንዲሁም በጥምረት አንድ ሺ ብር የሞራል ካሳ በድምሩ ሁለት ሚሊዮን አንድ ሺ ብር እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡