የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል በሁለትዮሽ ወታደራዊ ቴክኒካዊ ትብብር ወቅት የተገኙ የአዕምሯዊ የፈጠራ ሥራ ውጤቶችና ንብረቶች የጋራ ጥበቃ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ስምምነቱ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር የተፈረመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በሁለትዮሽ ወታደራዊ የቴክኒካል ትብብር ሂደቱ ውስጥ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መስክ የተሻለ የጋራ መግባባትና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ በኢትዮጵያና በሊባኖስ መንግሥታት መካከል በሥራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአፍሪካ መድሐኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ልኳል፡፡
በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን መንግስታት መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ንግድ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አዳምጦ ለንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በህንድ መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት ያግዛሉ የተባሉ አዋጆችንም መርምሮ አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም የምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔንም ምክር ቤቱ በስብሰባው መርምሮ ስለማፅደቁ ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
