በአሸናፊ አሰበ
ጥቅምት 3 ይመሰረታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የሐይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምስረታ የሚያቋቁሙት አካላት በምስረታው ሂደት ላይ አንዳንድ ስራዎች ቀርተውናል በማለታቸው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደሴ ከፍያለው ለአዲስ ጊዜ ገለጹ፡፡
ምክር ቤቱ የእርስ በእርስ ቁጥጥርን በሐይማኖት መገናኛ ብዙሀን መካከል ከማጠናከሩም ባሻገር እርስ በእርስ ለመተራረም፣ ዘርፉን ለማሳደግ፣ በጋራ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት እና ለመተባበር ታሳቢ ተደርጎ እንደሚቋቋም የገለጹት ዳይሬክተሩ ነገር ግን ምክር ቤቱን የማቋቋም ስልጣን የመገናኛ ብዙሀን መስሪያ ቤት አለመሆኑና ይህን የማድረግ ሀላፊነት ሙሉ በሙሉ የሃይማኖት ተቋማቱ የሚዲያ ኃላፊዎች እንደሆነ አቶ ደሴ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን የእርስ በእርስ ቁጥጥር ማለት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚገዙበት፣ የሙያ ስነምግባርና የመልካም አሰራር ደንብ የሚያወጡበት፣ የዘርፉን የሙያ ብቃት የሚያሳድጉበትና የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ቅሬታዎች የሚያስተናግዱበት አሰራር በመዘርጋት ራሳቸውን ለሕዝብ ተጠያቂ አድርገው እርስ በእርስ የሚተራረሙበት ሂደት መሆኑን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/13 ይገልጻል፡፡
በአንዳንድ የሐይማኖት ተቋማት ሚዲያዎች የሚታየውን ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶችን የማስተላለፍ እንቅስቃሴ ከመከላከል አኳያ የምክር ቤቱ ምስረታ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ስንል የጠየቅናቸው አቶ ደሴ ምክር ቤቱ ምን ምን ሥልጣኖች እንደሚኖሩት በምስረታው ወቅት እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ፍቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ 38 የመንፈሳዊ ቴሌቪዥን ሚዲያዎች የሚገኙ ሲሆን የሚቋቋመው ምክር ቤት ሁሉንም ቤተ እምነቶች ያካተተ እንደሚሆን አቶ ደሴ ከፍያለው ለአዲስ ጊዜ አስታውቀዋል፡፡
