በ-መርሻ ጥሩነህ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከሰሞኑ የቀይ ባህርን ጉዳይ በአደባባይ አጀንዳ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ኤርትራ ለጉዳዩ ምላሽ መግለጫ አውጥታለች፡፡
ኤርትራ በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው አጭር መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በባህር በር ጉዳይ እያራመዱት ያለው አቋም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ግራ ያጋባ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባህር በርና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የተነሳው አጀንዳ ሰፊና ከመጠን በላይ የተራገበ መሆኑንም ጠቁማለች፡፡ ሁኔታው ግራ እንዳጋባት የገለጸችው ኤርትራ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በጉዳዩ አጀንዳ መሆን አንዳይበሳጩ አሳስባለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተለያዩ አካላትን ስለ ጉዳዩ በማስረዳት ውስጥ ለውስጥ ሲያብላሉት ከርመው በይፋ አደባባይ ካወጡት በኋላ፣ ከኤርትራ በኩል ከፍተኛ ቁጣ ተሰምቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ በቀጥታ ስማቸው የተጠቀሱት እንደ ኤርትራ፣ ሶማሊና ጅቡቲ ያሉ አገራት ፖለቲከኞች እና ዲፕሎማቶች ሀሳባቸውን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከኤርትራ ኃይሎች በኩል በስፋት የተሰጠው ምላሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰቡት ሀሳብ ቅዥት እንደሆነ የሚገልጽና ኤርትራ ሉአላዊነቷን ለማስከበር አቅሟን አሟጣ ጦርነት ትገጥማለች የሚል ነው፡፡
እስካሁን ከተሰሙ ሀሳቦች መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀይ ባህር ጉዳይ ማብራሪያ ጎረቤት አገሮች ላይ ጥርጣሬ እና የግጭት ድባብ የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስ፣ በኤርትራ ሉአላዊነት ላይ የተቃጣ ስጋት መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡
ሕወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ውጊያ ላይ በነበሩበት ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ የኤርትራ ዲፕሎማቶችና ፖለቲከኞች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደከዷቸው እየገለጹ ነው፡፡
አምባሳደሮችን ጨምሮ በስፋት በተንጸባረቀው የኤርትራ ኃይሎች የቁጣ ስሜት፣ ኤርትራ ቀይ ባህርንም ይሁን አሰብን ለማንም አሳልፋ እንደማትሰጥ፣ አጀንዳውን ያመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩም የኢትዮጵያ ሕዝብም ቁርጡን ይወቀው እያሉ ነው፡፡
ከአረቡ እስከ ምዕራቡ ዓለም የተዘረጋ ውስብስብ ጂኦ-ፖለቲክስ አውድ የያዘው የያኔው የኢትዮጵያ ተፈጥሯአዊ የባህር በር ቀይ ባህር፣ ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች በኋላ ኢትዮጵያን የባህር በር የሌላት አገር አድርጓታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህር በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ አካል እንደነበር በመጥቀስ፣ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር በማገናኘት የይገባኛል ጥያቄ ማቅረብ አማራጭ የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጋሪ ካልሆነች ከሰላማዊ አማራጭ የተሻገረ ነገር ሊኖር እንደሚችል መግለጻቸው ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ የስጋት ምንጭ እንዲሆን አደርጎታል፡፡
ጉዳዩ አጀንዳ ከሆነ ወራቶች የተቆጠሩ ቢሆንም አሁን ላይ በይፋ አደባባይ መውጣቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የቀይ ባህር አጀንዳ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከወዲሁ የልዩነት ሀሳቦች መንጸባረቅ የጀመሩ ሲሆን፣ በአንድ በኩል ጊዜው አሁን አይደለም የሚል መከራከሪያ ሲሰማ በሌላ በኩል ደግሞ አጀንዳ መሆኑ ተገቢ ነው የሚሉ ወገኖችን እያወዛገበ ነው፡፡
