‹‹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ላይ የሚደርሰው ግፍ’ና መከራ ሃይማኖትን የሚያጠፋ የሃገር መሠረት የሆነውን እሴት የሚንድ ነው ›› – አቡነ ማትያስ

Addisgize

 በዳዊት ታደሰ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቤተክርስቲያኗ ለ42ኛ ጊዜ የምታካሂደውን አመታዊ ዓለማቀፍ ጉባኤ ተከትሎ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ‹‹ በቤተክርስቲያኗ፣ ምዕመኗ እንዲሁም አገልጋይ ካህናቶቿ ላይ የሚደረው ግፍና መከራ ሄዶ ሄዶ ሃይማኖትን የሚያጠፋ ነው ›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹ በቤተክርስቲያኗ ምዕመናን እና አገልጋይ ካህናቶቿ ላይ የሚደርሰው ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀል እና እንግልት ኢትዮጵያ አለኝ የምትለውን እሴት በማጥፋት ሃገሩን፣ ባህሉን፣ እሴቱን በጥቅሉ ማነንቱን የማያውቅ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል ›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ድርጊቱ ሃገሩን ባህሉን እሴቱን በጥቅሉ ኢትዮጵያዊ ማንነውቱን የማያውቅ ትውልድ እንደሚፈጠር የሚናገሩት አቡነ ማትያስ ይህ አይነቱ ትውልድ ከመፈጠሩ አስቀድሞ በጥንካሬ መስራት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

በምዕመናን ህልውና ላይ አብዝቶ መስራት እንደሚገባ የገለጹት ፓትርያርኩ  ሁሉም የሚኖረው ምዕመናን እስካሉ ድረስ ብቻ መሆኑን አንክሮ ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ የምዕመናን ህልውና ሁሉም የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ በትኩረት ሊገነዘበው እንደሚገባ አሳስበው ሊታለፍ የማይገባ አብይ ነጥብ የቤተክርስቲያኗ አንድነት ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ በቤተክርስቲያኗ አንድነት እና ቀኖናዊ ይዘቷ ላይ ጥያቄ ያለው ይኖራል ብለን አንገምትም ›› የሚሉት አቡነ ማትያስ ‹‹ በአስተዳደራዊ እና በዘመን ወለድ ቅሬታዎች የቤተክርስቲያኗ አንድነት እየተፈተነ ስለመሆኑ ›› አብራርተው ተናግረዋል፡፡

አክለውም በአስተዳደራዊ እና በዘመን ወለድ ቅሬታዎች የተፈተነው የቤተክርስቲያኗ አንድነት በውስጣቸው የተፈጠረ እንቅፋት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹ ቤተክርስቲያኗን እየፈተናት የሚገኘውን የአንድነት ፈተና በተለመደው መጽሃፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በጥበብ እና በብልሃት ማረም ግድ እንደሚላቸው ›› የገለፁት አቡነ ማትያስ ‹‹ ተላያይቶ መኖር ያሳፍራል፣ ያዳክማል እንጂ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል እና ብርታት  ሊሆን አይችልም ›› ብለዋል፡፡

ስለሆነም ቅሬታን በድርድር እና በውውይይት በይቅርታ እና በመተማመን ዘግቶ አንድነትን ማጽናት ይገባል ነው ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ፡፡