በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ነበር ። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ በማድረግ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ባለፉት 10 ወራት “የጅምላ ግድያ” ጨምሮ “ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል” ብለዋል፡፡ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች “ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል” ያሉት አቶ አበባው ለማሳያነትም በእርሳቸው ምርጫ ክልል ጅጋ፣ በፍኖተሰላም፣ በመርዓዊ፣ በደብረ ኤልያስ፣ በደብረሲና፣ ጎንደር እና ወሎ ተፈጽመዋል ያሏቸውን ግድያዎች ጠቅሰዋል። ጾታዊ ጥቃት እና ድብደባን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውንም አመልክተዋል።
በአማራ ተወላጆች ላይ ይፈጸማል ያሉትን “የጅምላ እስር” ጉዳይም አቶ አበባው አንስተዋል። አቶ አበባው “ለወራት በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ” ካሏቸው ውስጥ የምክር ቤት አባላት፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና አንቂዎች እንደሚገኙበት አብራርተው መንግስት “የህሊና እስረኞችን ለመፍታት፣ የጅምላ ግድያ እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን ወስኗል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድም ‹‹መንግስታችን እስረኛ መፍታት ላይ አይታማም ፤እንደውም እንዴት እስረኛ ትፈታለህ ተብለን ስንገመገም እና ስንወቀስ ነበር›› በማለት መልስ ሰጥተዋል። ‹‹ያልፈታነው ጉድ አለ እንዴ ? እስር ቤቱን በሩን ከፍተን ነው የለቀቅነው። በዚህ እንኳን አንታማም።›› ሲሉ ተሟግተዋል፡፡
‹‹ከዚህ ፓርላማ የታሰሩት ወንድማችንን በተመለከተ (አቶ ክርስቲያንን ለማለት ነው) ሁሉም ተቃዋሚ የሚታሰር ከሆነ ጠያቂዬ ለምን አልታሰሩም ? ጠያቂዬ ተቀምጠው እየጠየቁ ነው›› ሲሉ አስተባብለዋል። ‹‹እርሶን የሚያስቀምጥ እሳቸውን የሚያሳስር ነገር ካለ ልዩነት አለ ማለት ነው። ልዩነቱን ግን እኔ ዳኛ አይደለሁም ወንጀለኛ ናቸው ጥፋተኛ ናቸው ልል አልችልም። የፍትሕ ስርዓቱ አይቶ መርምሮ ፈትሾ ፍርድ ይስጥ።›› ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ‹‹ በሰላማዊ መንገድ 4 ኪሎ ተቀምጦ ‹ጉዞ ወደ 4 ኪሎ› ከሚሉ 4 ኪሎ ተቀምጠው ጉዞ ወደ ፓርላማ እያሉ በሰላም ቢታገሉ ችግር የለብኝም ›› ብለዋል።
‹‹አቶ ክርስትያንን ህግ ከፈታቸው ከእኛ መካከል ቢሆኑ ደስታውን አልችለውም ፤ነገር ግን ሁላችንም ማወቅ ያለብን የፓርላማ አባል መሆን ፣ጋዜጠኛ መሆን ፣ሚኒስትር መሆን ፣ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆን ከወንጀል እና ከጥፋት አይታደገንም። አለማጥፋት ነው። የኔ ዋስትና አለማጥፋት ነው፤ ካጠፋሁ እመጣለሁ ያለመከሰስ መብቴ ይነሳል እጠየቃለሁ።›› ብለዋል፡፡

በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን በተመለከተም ‹‹ዝም ብሎ መንገደኛ ይነሳና ዩቲዩብ ከፍቶ ነው ጋዜጠኛ ነኝ የሚለው እንደዛ ትክክል አይደለም።ጋዜጠኛም ህግ አለው ፣ ወታደርም ቢሆን ህግ አለው መጠየቅ አለበት ፣ ሚኒስትርም ህግ አለው። በዚህ አግባብ ማየት ካልቻልን ስራችንን ቆርጠን ጥለነው በኋላ የማንጠግነው ነገር ይፈጠራል። ” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንፈቅለ መንግስት ለማድረግ “ውይይት የሚያደርጉ” አካላት እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ‹‹መፈንቅለ መንግስት አይሳካም፤ እኛ ወታደሮች ነን መፈንቅለ መንግስት እንዳይሳካ አድርገን ነው ተቋማት የሰራነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
“በርካታ ሰዎች በነዋይ ፍቅር ሰክረዋል። ያ የነዋይ ፍቅራቸውን ለመመለስ የመጨረሻው ግብ ስልጣን መያዝ ነው ብለው ያስባሉ። እኔ ካልሆንኩ በቀር ይላሉ” ያሉት ዐብይ፤ “በቅርቡ መፈንቅለ መንግስት እናካሄዳለን” በሚል ውይይት የጀመሩ ግለሰቦች እንዳሉ ተናግረዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ውይይት ያደርጋሉ ያሏቸውን አካላት በግልጽ አላሳወቁም።
“ኢትዮጵያ ውስጥ መፈንቅለ መንግስት አንዴ የዛሬ 50 ዓመት ተሳካ፤ ከ50 ዓመት በኋላ ብዙ የሚረቡና የማይረቡ ሙከራዎች ነበሩ አልተሳኩም። አሁን ጭራሽ አይሳካም ›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለወንድሞቼና ታላላቆቼ ምክር መስጠት እፈልጋለሁ ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ‹‹የወዳጆቻችንን ሀገር ገንዘብም አታባክኑ፣ ገስት ሀውስም አታጣቡ አይሳካም ›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡አክለውም ‹‹በግጭት ፣ በጦርነት ፣ በሽፍታነት ፣ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ መያዝ ማለት ብሎን እንደ ተበላበት ጥርስ ማለት ነው ፤ የሚሽከረከር እንጂ የማይሻገር ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐብይ ‹‹በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ምክር ስንለግስ ቀለል አድርገው የሄዱ ሰዎች በኋላ ዋጋ ይከፍላሉ።›› ብለዋል፡፡
