በቱርክ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባቶችን በሰላም እንደሚፈቱ ገለጹ

ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ  ከስድስት ወራት በፊት  የባህር በር መግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ነበር ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ  ውዝግብ ውስጥ የገቡት፡፡ በዚህም ምክንያት ሰኔ 24/ 2016 ዓ.ም በቱርክ ጋባዥነት ለመጀመሪያ ጊዜ በመሃላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ዙሪያ ለመነጋገር  ወደ ቱርክ   አንካራ ያቀኑት ኢትዮጵያና ሶማሊያ  በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም ከውይይታቸው በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው ይህንን ያስታወቁት።

በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን አመቻችነት የተገናኙት የሁለቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች  ያላቸውን ልዩነቶች ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ያሉ ሁኔታዎችን እንደዳሰሱም የሶስቱ አገራት የጋራ መግለጫ አትቷል።

ሁለቱ አገራት መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ሚኒስትሮቹ ለሁለተኛ ዙር ውይይት በአንካራ ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም እንደሚገናኙ ተገልጿል።

የሶስቱ አገራት የጋራ መግለጫ ሁለቱ አገራት ልዩነታቸውን ለሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንደዳሰሰ ቢገልጽም  ተቀባይነት አላቸው የተባሉት ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በግልፅ አልጠቀሰም፡፡

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ አንካራ ማቅናታቸውን በመግለፅ   “የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የግዛት አንድነትን የመጠበቅ መርህ ላይ ቁርጠኛ ነን ” ብለዋል።ስለ ስምምነቱ ግን ዝርዝር ሃሳቦችን ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የኢትዪጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራቱን የጋራ መግለጫ ይፋዊ በሆነው ገጹ አውጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ሰፈር በኪራይ የምታገኝበት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥበት ስምምነት በሁለት ወራት ገደማ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ከሳምንታት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቷታል፡፡ በቀጠናውም  ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል።

ሶማሊያ ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎችን ከማውጣት በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።

በቅርቡም ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሕገወጥ መልኩ ድንበር ተሻግረው ወደ ሶማሊያ ገብተዋል ስትል ለተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ከሳለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ ሶማሊያ ያቀረበችው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ስትል አጣጥላለች።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች  ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንዲወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ አስጠንቅቀዋል።

ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል ወታደሮቿን በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኘው ኢትዮጵያ በበኩሏ ወታደሯቿን እንድታስወጣ ከተፈለገ በይፋ ጥያቄው ሲቀርብ ተግባራዊ እንደሚሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ጠቁመው “ከሶማሊያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ከተባበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለውን ኃይሏን ታስወጣ የሚል በይፋ የቀረበ ነገር የለም” ብለዋል።