የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በመንግስት ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መንግስት ከፍተኛ ጥቃትና ጫና እየፈጸመበት እንደሆነ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

ኢሰመጎ በመግለጫው በመንግስት እየደረሰበት ያለው ጥቃት እና ጫና አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን  አሳውቋል።

ጉባኤው በተለያዩ ጊዜ ተፈጽመውብኛል ያላቸው ጥቃቶች እና ከፍተኛ ጫናዎች በመግለጫው ላይ የዘረዘረ ሲሆን በተቋሙ አመራር ላይ በመንግስት የደህንነት ሰዎች የሚፈጸም ክትትል ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየጨመረ መምጣታቸውን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ክትትል ስራችሁን ካላቆማችሁ ፤ መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት መወንጀል ካላቆማችሁ  ‘ ዋጋ ትከፍላላችሁ ‘ የሚል ዛቻ እየደረሰበት መሆኑን ገልጿል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ስራ በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ የመንግስት ጸጥታ አካላት አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ መሳደብ፣ ማንገላታት፣ ስራቸውን እንዲያቆሙ ማስፈራራት እየሰረሰባቸው  እንደሆነም ድርጅቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

 ኢሰመጉ ላለፉት 32 ዓመታት በሀገሪቱ ህግ አግባብ ተመዝግቦ እየሰራ ያለ ተቋም ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል ግን  በጸጥታ ሰዎች ” ፍቃድ የላችሁም ” በማለት ማስፈራሪያና የእስር ዛቻ እየተሰነዘረበት እንደሆነም አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የድርጅቱ አባላት ላይ ከህግ ውጭ እስር መፈጸም እና ወደ ፍርድ ቤት አለማቅረብን ጨምሮ በተለይም በአዲስ አበባ ተገቢ ያልሆኑ ክሶችን ለመመስረት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩብኝ ነውም ብሏል፡፡

የኢሰመጉ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ከሀገር ውጭ ካሉት ስራዎችና ስብሰባዎች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ እንግልት እና ማዋከብ  ፣ ማዋከብ እየደረሰባቸውም ነው ብሏል፡፡