የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል የኪነ ጥበብ ስራዎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጫ መንገድ በመሆናቸው ከጥቃት ሊጠበቁ እና ባለሙያዎችም ለእስር ሊዳረጉ አይገባም ብለዋል፡፡
መንግስት ለኪነ ጥበብ ሙያ እና ባለሙያዎች ልዩ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ ያሬድ ኪነ-ጥበብ ለሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ መዳበር፣ መጎልበት እንዲሁም መስፋፋት እና መከበር ያለው ጉልህ ሚና እጅግ የላቀ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች እና ባለሞያዎች በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በግጥም፣ በስዕል እና በቅርፃቅርፅ መልክ የሚያንጸባርቋቸው ሃሳቦች የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መገለጫዎች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እነዚህ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ለአንድ ማህበረሰብ የደስታም ሆነ የብሶት ሃሳቦቹን የሚገልጽባቸው መንገዶች የመሆናቸውን ያህል በአገር አስተዳደር ኃላፊነት ላይ ለተቀመጡ ወይም ለመንግስት አካላት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄዎች፣ ስጋቶች፣ እርካታዎች ወይም ብሶቶችን በማድረስም ረገድ ልክ እንደ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና የጥበብ ሥራዎች ወይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮችና ጫናዎች ከዕለት ዕለት እየበረቱ መምጣታቸው ድርጅታችንን ያሳስበዋል ብለዋል፡፡
ከነዚህም ውስጥ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ወቅታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ተከታታይ “ቧለቲካ” የቴአትር መድረክን፣በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት “እብደት በህብረት” የተሰኘው የመድረክ ተውኔት አዘጋጅና ተዋናይ ባለሙያዎች መታሰራቸውን ድርጅቱ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም የተለያዩ እንደ ስነ-ፅሁፍ፣ ተውኔት እና የመሳሰሉት ስራዎች የሚቀርቡባቸው የጥበብ መድረኮች የስብሰባ ፍቃድ ያስፈልጋችኋል በሚል እየተስተጓጎሉ ነውም ብሏል፡፡
መንግስት በህገ-መንግስቱ እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ የተደረገለትን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲያከብር እና በዘፈቀደ እንዳይጣስም ጥበቃ እንዲያደርግ፤ መንግስት ጥበብ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እና ፖለቲካዊ እድገት ያለውን ፋይዳ ከግንዛቤ በማስገባት ለጥበብ ባለሙያዎች እና ስራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ምህዳሩን በማስፋት ሀላፊነቱን እንዲወጣም ማዕከሉ ጠይቋል፡፡
እንዲሁም በሥራቸው ምክንያት የታሰሩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከእስር እንዲፈቱ ወይም የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙና የተከለከሉ የኪነ-ጥበብ መድረኮችም በነጻነት እንዲሰሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
